የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የትምህርት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ እና ጥራትን እንዲያስጠብቁ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው - የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የትምህርት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ እና ጥራትን እንዲያስጠብቁ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው - የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ መጋቢት 2/2015 (ኢዜአ)፦ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የትምህርት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ እና ጥራትን እነዲያስጠብቁ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆችን የትምህርት ጥራት ማሻሻል የሚችሉ አሰልጣኝ መምህራንን በማፍራት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ድጋፍ እያደረገ እየተደረገ መሆኑንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የአካዳሚክ ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ሐብቶም ገብረእግዚአብሔር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ብቃት ያላቸው የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኝ መምህራን እያፈራ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት ፍላጎትን መሰረተ ያደረገ በተለያዩ ዘርፎች የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግርም በአምራች፣ በግብርና፣ በኤሌክትሪካል፣ በጨርቃጨርቅ፣ በቱሪዝም እና አገልግሎት ዘርፍን ጨምሮ በሌሎች የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ ለአሰልጣኝ መምህራን እየሰጠ በሚገኘው ስልጠና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚፈልጉትን ብቁ የሰው ኃይል እያቀረበ ይገኛል ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ።
በስልጠናው ብቁ አሰልጣኝ መምህራንን በማፍራት ኮሌጆቻቸው ለሚሰጡት የስልጠና ፕሮግራም አጋዥ የሚሆን የአቅም ግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ኢንዱስትሪ የሚፈልገውን የስልጠና ቁሳቁስ በመያዝ ክህሎት እና ብቃትን ማሳደግ የሚያስችል የተግባርና የንድፈ-ሃሳብ ትምህርት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ለሰልጣኞች የብቃት ማረጋገጫ እየሰጠ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሐብቶም ለኢንስቲትዩቱ መምህራንም በአገር ውስጥ እና በውጭ የትምህርት ዕድል በማመቻቸት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ለአገር ውስጥ አሰልጣኝ መምህራን ከሚሰጠው ስልጠና በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ ከደቡብ ሱዳን እና ሶማሌላንድ ለመጡ ተማሪዎች የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢንስቲትዮቱ የምስራቅ አፍሪካ የቴክኒክ እና ሙያ የልህቀት ማዕከል ማድረግ የሚያስችል ዓላማ ይዞ እየሰራ ነው ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር ሐብቶም።
የኢንስቲትዩቱ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና መምህራን የቴክኒክ እና ሙያ ኢንዱስትሪ የሚፈልገውን የንድፈ-ሃሳብ ትምህርት በተግባር በማስደገፍ ብቁ የሆኑ አሰልጣኝ መምህራን እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢንስቲትዩቱ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ እየተሰጠ የሚገኘው የተግባር እና የንድፈ-ሃሳብ ትምህርት የተሻለ ክህሎት እንዲኖራቸው እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደመጡበት ኮሌጅ ሲመለሱም ተማሪዎች የተሻለ ክህሎትና እውቀት ይዘው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የአሰልጣኝ መምህራን ስልጠናን ጨምሮ የተለያየ የረጅም እና የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።
ኢንስቲትዩቱ ከዋና ግቢው በተጨማሪ ባሉት ከ15 በላይ ካምፓሶቹ እና በክልሎች በሚገኙ ቅርንጫፎቹ ከ13ሺህ በላይ አሰልጣኝ መምህራንን ጨምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል።