ቀጥታ፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ112 ሚሊየን ብር በላይ ማሰባሰቡን ገለጸ

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2015(ኢዜአ)፦ የቦሌ ክፍለ ከተማ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ112 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታወቀ።

ክፍለ ከተማው "ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሃብት ማሰባሰብ ዛሬም ዝግጁ ነኝ" በሚል መሪ ሀሳብ ግድቡ ሲጠናቀቅ በሚያመነጨው 5ሺህ 150 ሜጋ ዋት የሰየመውን "ቦሌ 5150" የአምስት ኪሎ ሜትር የዱላ ቅብብል ሩጫ ዛሬ አካሄዷል።


 

ውድድሩ የተካሔደው ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እስከ 24 ሜዳ ድረስ ባለው መስመር ሲሆን በክፍለ ከተማው ከሚገኙ 11 ወረዳዎች የተወጣጡ ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አለምፀሐይ ሽፈራው በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የክፍለ ከተማው ነዋሪ ለሕዳሴ ግድብ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡


 

በ2015 በጀት ዓመት በክፍለ ከተማ ደረጃ 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ በስምንት ወራት ብቻ በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ112 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።


 

"እቅዳችንን ቀድመን አጠናቀቅን ብለን ኃብት ማሰባሰባችንን አናቆምም፤ ግድቡ እስከሚያልቅ ድረስ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እናስቀጠላለን" ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ በበኩላቸው የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ላደረገው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


 

የውድድር ተሳታፊ ወጣቶች በበኩላቸው "ሃብታችንና እውቀታችንን ያለምንም ስስት የአንድነታችን ምልክት ለሆነው ህዳሴ ግድብ ግንባታ እናውላለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም