የኢትዮጵያ እግር ኳስን ለማሳደግ ታዳጊዎችን ማብቃት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እግር ኳስን ለማሳደግ ታዳጊዎችን ማብቃት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ መጋቢት 2/2015(ኢዜአ):- ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ታዳጊዎችን በእግር ኳስ ክህሎት ማብቃት ላይ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ለዚህም የሚረዳ የስልጠና መርሐ-ግብርን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከመሰረቱት አገራት መካከል አንዷ ብትሆንም የእግር ኳስ እድገቷ ግን በሚፈለገው ደረጃ ላይ መቀመጥ አልቻለም።
ለዚህም የዘርፉ ባለሙያዎች የአደረጃጀት ችግርን፣ የስልጠና ሁኔታን እንዲሁም በቂ የማዘውተሪያ ስፍራዎች አለመኖርን በምክንያትነት ያቀርባሉ።
ችግሮቹ የኢትዮጵያን እግር ኳስ በአፍሪካ ደረጃ በሚጠበቀው መልኩ ተፎካካሪ እና እድገት እንዳያሳይ ማድረጉን በማከል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፤ ፌዴሬሽኑ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ታዳጊዎችን ማብቃት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ብቁ እና ጠንካራ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እንዲኖራት ለማድረግ ዘመኑ የደረሰበትንና አሁናዊ ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ስልጠና መስጠት ጨምሮ ሌሎች ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ በተያዘው ዓመት 'ስሪ ፖይንት' ከተባለ የጀርመን ድርጅት ጋር በመተባበር "ዘመኑን የዋጀ" የታዳጊዎች ስልጠና መስጠት ጀምሯል ብለዋል።
በዚህም 30 ታዳጊዎች ተመልምለው በአዲስ አበባ የካፍ የልህቀት አካዳሚ ከጀርመን እና እንግሊዝ በመጡ እና በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የረጅም ጊዜ ስልጠና በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ነው አቶ ባህሩ የገለጹት።
ስልጠናውን የሚከታተሉ ሰልጣኞች በየጊዜው እየተመዘኑ ብቁ የሆኑት ወደ ክለቦች እንደሚዘዋወሩና የአቅም ክፍተት ያለባቸው ታዳጊዎች ደግሞ በሌሎች እንደሚተኩ ተናግረዋል።
በስልጠናው እየተካፈሉ ያሉ ታዳጊዎች ከእግር ኳስ ስልጠና ጎን ለጎን መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውንም አንስተዋል።
የስልጠናው ዋነኛ ዓላማ ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ እድገት መሰረት ለማኖር በታዳጊዎች ላይ ያተኮረ ዘመናዊ ስልጠና መስጠት መሆኑንና ይሄም ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ያግዛል ነው ያሉት።
የታዳጊዎችን የእግር ኳስ የክህሎት ብቃት በማሳደግ ብቁ እና ተመራጭ ሆነው በአውሮፓ እና ሌሎችም አገራት የመጫወት እድል አግኝተው ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ ሌላኛው የስልጠናው አላማ ነው ብለዋል።
የጀርመኑ 'ስሪ ፖይንት' የተሰኘው ድርጅት ታዳጊዎችን ካሰለጠነ በኋላ በብቃታቸው ተመርጠው በውጭ እና በሀገር ውስጥ በሚገኙ ክለቦች ተዘዋውረው የመጫወት እድል ሲያገኙ ከሚገኘው ገቢ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ጥቅሞችን እንደሚጋራ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።