የተማሪዎች ምገባ መርሃ-ግብር ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ቀንሷል፤ ውጤታቸውንም አሻሽሏል--የደብረ ብርሃን ከተማ ትምህርት መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
የተማሪዎች ምገባ መርሃ-ግብር ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ቀንሷል፤ ውጤታቸውንም አሻሽሏል--የደብረ ብርሃን ከተማ ትምህርት መምሪያ

ደብረብርሃን መጋቢት 2/2015 (ኢዜአ):- በደብረ ብርሃን ከተማ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የምገባ መርሃ-ግብር ተማሪዎች ትምህርታቸውን በትጋት እንዲከታተሉና ውጤታቸውን እንዲያሻሽሉ አስተዋጽኦ ማድረጉን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ተክለዮሐንስ ኃይለጊዮርጊስ እንደገለጹት፣ በከተማው በአራት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች ምገባ መርሃ-ግብር እየተከናወነ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ 2ሺህ 17 ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ለመርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ 10 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ተናግረዋል።
መርሃ-ግብሩ የተማሪዎችን ትምህርት የማቋረጥ መጠን ከመቀነስ በላይ ውጤታቸው እንዲሻሻል ማገዙንም ገልጸዋል።
በቀጣይ ዓመት የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩን በ77 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለማስፋፋት ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው አመልክተዋል።
በደብረ ብርሀን ከተማ የአንድነት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህር ባዩ ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ምገባ በጥቅምት ወር 2015 ከተጀመረ ወዲህ ትምህርት የሚያቋርጥ ተማሪ እንደሌለ ገልጸዋል።
ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው በመማራቸው የንባብ ባህልን ከማዳበር ባለፈ ውጤታቸውና ባህሪያቸው እየተሻሻለ እንዲመጣ ማድረጉንም ርዕሰ-መምህሩ ጠቁመዋል።
አቶ በላይነህ ታችበል የተባሉ የተማሪ ወላጅ በበኩላቸው በአናፂነት ሙያ በቀን ሥራ በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ሦስት ልጆቻቸውን ለማስተማር ከብዷቸው እንደነበር ገልጸዋል።
መንግስት በትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ በመጀመር እያደረገ ያለው ድጋፍ ትልቅ እፎይታ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
የምገባ መርሃ-ግበሩ የብዙ ችግረኛ ወላጆችን የኑሮ ጫና ስላቃለለ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ በላይነህ ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ከ200ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።