ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከተርኪዬ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት ቁርጠኛ ናት - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከተርኪዬ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ እና ስትራቴጂካዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

አቶ ደመቀ የስራ ጊዜያቸውን አጠናቀው ከተሰናበቱት በኢትዮጵያ የተርኪዬ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ ጋር ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደሯ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲጠናከር ለነበራቸው ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


 

ኢትዮጵያ ከተርኪዬ ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።

ተሰናባቿ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት በተርኪዬ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የነፍስ አድን ቡድን በመላክ ላሳዩት አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ተርኪዬ በኢትዮጵያ በምታደርገው የኢንቨስትመንት መጠን በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች ያሉት አምባሳደሯ አገራቸው ከኢትዮጵያ በንግድና ኢኮኖሚ መስኮች ያላትን ትስስር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም