ቀጥታ፡

አምባሳደር ሂሩት ዘመነ የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳዮች አገልግሎት የፖለቲካ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሐፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2015 (ኢዜአ)፦ በቤልጂየም፣ ሉክሰምበርግ እና የአውሮፓ ሕብረት ተቋማት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ከአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳዮች አገልግሎት የፖለቲካ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሐፊ ኤነሪኬ ሞያ ጋር ውይይት አደረጉ።

የውይይታቸው ትኩረትም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በሕብረቱ መካከል ያለውን ግንኙነት  በአዲስ መልክ ማደስ በሚቻልበት ላይ መክረዋል።

አምባሳደር ሂሩት ስለ ሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ፣ የሰላም ስምምነቱ አሁን ያለበትን ደረጃ እና የአገራዊ ምክክር ዝግጅትን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳዮች አገልግሎት የፖለቲካ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሐፊ ኤንሪኬ ሞራ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በቅርብ ለመከታተል ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በአገሪቱ መሬት ያለውን እውነታ ለማወቅ እንደሚያግዛቸው መግለጻቸውን በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም