ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች የህብረተሰቡን ምርታማነት እያሳደጉ ያሉ አነስተኛ የመስኖ ልማቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል--ዶክተር ግርማ አመንቴ      

ድሬደዋ (ኢዜአ) መጋቢት 1/2015 በግብርና ልማት ሁለተኛው መርሃግብር በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች የህብረተሰቡን ምርታማነት እያሳደጉ ያሉ አነስተኛ የመስኖ ልማቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ አሳሰቡ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የድሬዳዋ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በመስኖ ልማት በመታገዝ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ መሆኑን ገልፀዋል።

በሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ የተመራውና የዓለም ባንክና የዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ተቋማት ተወካዮችን ያካተተው ልዑካን ቡድን በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች በግብርና ዕድገት ሁለተኛው መርሃግብር የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተመልክቷል።

በእዚሁ ጊዜ የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ እንደተናገሩት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግስት  ከዓለም ባንክ እና ከግብረ ሰናይ ተቋማት ጋር በመተባበር በመላው አገሪቱ ያከናወናቸው የልማት ሥራዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ እያገዙ ናቸው።

በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች በአነስተኛ መስኖ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ አሻራና መሰል እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች የሚበረታቱና ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተለይ ትላንት በይፋ የተጀመረውና የግብርና ዕድገት ሁለተኛው መርሃግብር ቀጣይ የሆነው ፕሮጀክት የተጀመሩትን ሥራዎች የሚያሳድግና በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የገጠሩ ማህበረሰብ በተገነቡ የግብርና ልማቶች ዘላቂ ተጠቃሚ እንዲሆን የልማት አውታሮችን በጥንቃቄ መያዝና መንከባከብ እንዳለበትም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው በግብርና ዕድገት ሁለተኛው ምዕራፍ በብዙ ሚሊዮን ብር ወጪ አነስተኛ መስኖዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

የመስኖ ልማቶቹ የነዋሪውን የገቢ ምንጭ በማሳደግ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ እያስቻሉ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለእዚህም በዱጅማ ገጠር ቀበሌ በሦስት ሚሊዮን ብር የተገነባው አነስተኛ የመስኖና የውሃ መውረጃ ካናል 191 ቤተሰቦች 48 ሄክታር መሬት አልምተው የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ማገዙን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

"በተመለከትኳቸው የልማት ሥራዎች እና አርሶ አደሮቹ ለመለወጥ በሚያሳዩት ጥንካሬ ተደስቻለሁ" ያሉት ደግሞ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ኦስማኔ ዲኦኔ ናቸው።

በቅንጅት የተጀመረው ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ በትጋት መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የድጁማ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ በግብርና ዕድገት ሁለተኛው መርሃግብር የተሰሩላቸው የመስኖ ልማቶች ምርት ምርታማነትን በማሳደግ ከነበረባቸው ችግር እንዲላቀቁ እያገዟቸው ነው።

አርሶ አደር አብደላ መሀመድ እንደገለጹት፤ የመስኖው ውሃ እንዳይባክን የተገነባው ሁለት ኪሎ ሜትር የውሃ መውረጃ ካናል ውሃን በፈረቃ እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል። 

እያንዳንዱ አባወራ አርሶ አደር በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት በትንሹ እስከ 150ሺህ ብር እንዲያገኝ ማድረጉንም ገልጸዋል።

"ይህን ጥቅም ዘላቂ ለማድረግ ለመስኖ ፕሮጀክቱ ተገቢውን እንክብካቤ እና ጥበቃ እያደረግን ነው" ብለዋል።

"በተሠራው የመስኖ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ እና ፍራፍሬ እያመረትኩ ነው" ያሉት ደግሞ አርሶ አደር መሐመድ አደም ናቸው።

በአንድ የምርት ወቅት ብቻ ከቲማቲም ምርት ሽያጭ እስከ 30ሺህ ብር ማግኘታቸውን ገልፀው፣ "ይህም የቤተሰቤን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አስችሎኛል" ብለዋል። 

ወጣት አርሶ አደር ኢሊያስ አህመድ በበኩሉ ሥራ የሌላቸው የቀበሌው ወጣቶች በመደራጀት ነጎርፍ ይጠረግ የነበረን መሬት ወደ እርሻ በመቀየር የልማቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግሯል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም