ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ጃፓን የ25 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

 አዲስ አበባ /ኢዜአ/ መጋቢት1/2015  ኢትዮጵያና ጃፓን የ25 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ተፈራርመዋል፡፡

ከድጋፍ ስምምነቱ ውስጥ 20 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላሩ ለንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሁም  ቀሪው 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላሩ ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡

በዚህም በአጠቃላይ ከ217 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም 2 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም እንደሚውል ተገልጿል፡፡


 

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በዚሁ ጊዜ፤ የድጋፍ ስምምነቱ በኢትዮጵያና ጃፓን መካከል ያለውን ወዳጅነት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ድጋፉ የኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት በማገዝ ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን እንደሚያግዝ  ተናግረዋል፡፡

ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ የተደረገው የድጋፍም ስምምነት ጃፓን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የምግብ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የምታደርገው እገዛ አካል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታዋ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው ድጋፉ መንግስት ለዜጎቹ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም የግብርና ዘርፉን ለማጎልበት የሚያከናውናቸውን ስራዎች እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጂኦ-ፖለቲካና ኢኮኖሚ መስኮች እየተዩ ያሉ አለመረጋጋቶች አንጻር የድጋፉ ስምምነቱ ለኢትዮጵዯ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም