ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል ስምንት ከተሞች የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ  አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ

ጅግጅጋ፤ መጋቢት 1ቀን  2015 (ኢዜአ) ፡-   በሶማሌ ክልል  ስምንት የዞን እና ወረዳ ከተሞች የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ የኤሌክትሪከ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት አስታወቀ። 

በዶሎ፣ ቆረሃይ፣ ሸበሌና ፋፈን ዞኖች የሚገኙ የዋርዴር፣ ኩዱንቡር፣ ይዒብ ፣ገርሎጉበይ፣ ዋፍዱብ ኢልሓር፣ በራጂሳሌ እና አፉፍሌይ ከተሞች ናቸው አገልግሎቱን ያገኙት።

የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ አገልግሎት የሶማሌ ሪጅን ፕሮጀክት አስተዳደር ኃላፊ አቶ አሊ ሰዒድ ከመንግስት በተመደበ 200 ሚሊዮን ብር ባለፉት ስድስት ወራት የሙሉ ቀን የኤሌትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ሲሰራ መቆየቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በሃይድሮ  የኃይል ማመንጫ 207 ኪሎ ሜትር መስመር በመዘርጋት እና 2 ሺህ 217 ምሶሶ ተከላ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል። 

የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል 18 ትራስፎርመርም በከተሞቹ መተከሉን በመጠቆም። 

ከተሞቹ የ24 ሰአት የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት እንዲያገኙ ከክልሉ መስተዳድር አካላት እና ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራቱ ውጤታማ ማድረግ መቻሉንም ነው አቶ አሊ የገለጹት።

የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦቱን በሌሎች 11 ከተሞች እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለማደረስ መታቃዱንና ዜጎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የመስመር መዘርጋት ጨምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።


 

በዋርዴር ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ነዋሪዎች መካከል አቶ አብዲላሂ መሐመድ በሰጡት አስተያየት፤ የመብራት ተጠቃሚ በመሆናቸው ለዘመናት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲመቻችላቸው ሲያቀርቡት ነበረው ጥያቄ ምላሽ በማግኘታቸው ችግራቸው መቃለሉን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ከተማ በሸቀጣሸጥ ንግድ የተሰማሩት አቶ አብዲከሪም አዊል በበኩላቸው፤ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማገኘታቸው በኑሯቸውና በንግድ ስራቸው ላይ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል ፡፡

"መብራት በማገኘታችን ቀንና ሌሊት መስራት በንግድ ስራዬ ላይ የተሻለ ገቢ ማገኘት ችያለሁ " ብለዋል።

የመብራት አገልግሎት በመዘርጋቱ ልጆቻችን ትምህርታቸውን ያለችግር ለማጥናት ከመቻላቸውም በላይ በኩራዝ ጭስ ምክንያት በጤናችን ላይ ከሚደርሰን ጉዳት ተላቀናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ንምዓ አው አህመድ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ፕሮጀክት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በክልሉ ብዛት ያላቸው የዞንና የወረዳ ከተሞች ከሀይድሮ የሃይል ማመንጫ የ24 ሰዓት ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከፕሮጀክቱ አስተዳደር ኃላፊ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም