ቀጥታ፡

የባህል ስፖርቶች ውድድርና የባህል ፌስቲቫል ሊጠፉ የሚችሉ መልካም የኢትዮጵያ ባህሎችን የሚታደግ ነው

ሚዛን አማን (ኢዜአ) መጋቢት 01 ቀን 2015 የባህል ስፖርቶች ውድድርና  ፌስቲቫሎች  የኢትዮጵያን ባህሎች ከመጥፋት የሚታደጉ ኩነቶች በመሆናቸው  እንዲጠናከሩ የበኩላቸውን አንደሚወጡ  የተለያዩ ክልሎች  የስፖርት የባህል ልዑካን ቡድን አባላት አስታወቁ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው 20ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ዉድድርና 16ኛ የባህል ፌስቲቫል የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ጎልተው እየታዩ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሳታፊ የባህል ልዑካን ቡድን ለማህበራዊ መስተጋብርና ለጠንካራ አንድነት መሰሶ የሆኑ ባህሎች በመጤ ባህሎች ተወርረው እንዳይጠፉ በማስተዋወቅና በማሸጋገር ረገድ ኩነቱ የጎላ ድርሻ እንዳለው አስገንዝበዋል።

ልዑካኑ ባህላዊ ሥርዓቶችን በዓመት አንድ ጊዜ ለእይታ ከማብቃት ባሻገር በዘወትር ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በማንጸባረቅ ሊጎለብቱ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኙት አቶ እንድሪስ መሐመድ እንዳሉት ዓመታዊ ፌስቲቫሉ የመጥፋት ስጋት የተደቀነባቸውን የተለያዩ ብሔረሰቦችን ባህሎች እየታደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በየክልሎች ውስጥ የሚገኙ ባህላዊ ሥርዓቶችን ልምድ መለዋወጥ መቻላችን የኢትዮጵያን ሙሉ ገጽታ እንድናውቅ የሚረዳ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።

በፌደራል ደረጃ የሚካሄደው የባህል ስፖርቶች ውድድርና የባህል ፌስቲቫል እንደተጠበቀ ሆኖ ክልሎች በውስጣቸው የያዟቸው ባህሎች እንዲጎለብቱ ለማድረግ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ድምር ውጤት በመሆኗ የዜጎችን መልካም የሆኑ ባህሎች ሳያበላልጡ እኩል ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አቶ እንድሪስ አመላክተዋል።

ከአፋር ክልል የመጡት አቶ ዑመር ዓሊ በበኩላቸው የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫሉ ኢትዮጵያዊነት ፍቅርና ሰላም መሆኑን ያየንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የሌለን የሚመስለን በርካታ ትልቅ የሚያደርገን ባህል፣ ወግና ሥርዓት ያለን ህዝቦች ነን ያሉት አቶ ዑመር፤ እነዚህን በጎ ባህላዊ ክዋኔዎችን የማልማት ሥራ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

ከተለያዩ አካባቢ ከመጡ ኢትዮጵያውያን ጋር በባህላዊ ክዋኔ መድረክ ላይ መገናኘት ከልምድ ልውውጥ ባሻገር የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያስችል የአንድነት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

ባህላችን ዘላቂ ሆኖ በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲቆይ አሁን ላይ ጥሩ ሥራ እንደ ሀገር እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል ቡድን ልዑክ አባል አቶ ብርሃኑ አድማሱ ናቸው።

ለአብነትም በመዋቅር ደረጃ ከፌዴራል ጀምሮ ባለቤት እንዲኖረው መደረጉንና አሁን ደግሞ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ማካተት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባህሎች በተለያዩ ጥናቶች፣ አውደ ርእይ እና ሲምፖዚየሞች አማካይነት ተደግፈው እያደጉ በመምጣት ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ያላቸው ሚና ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ጠቁመዋል።

ማንነታችንን ለዓለም የምንገልጸው በባህል ወጋችን እንጂ በዘመናዊው የውሰት ማንነት ያለመሆኑን በመረዳት ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ነው ያሉት።

በዓመት አንድ ጊዜ በፌስቲቫል ለእይታ ከማብቃት ባሻገር ባህላችንን በዘወትር ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎቻችን ውስጥ በማንጸባረቅ ልናጎለብት እንደሚገባም ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም