የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሲንጋፖር በድጋሚ የቀጥታ በረራ ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሲንጋፖር በድጋሚ የቀጥታ በረራ ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 1/2015 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ሲንጋፖር አቋርጦት የነበረውን የቀጥታ በረራ በድጋሚ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
በረራው መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚጀመር እና በሳምንት አራት ጊዜ አገልግሎቱን እንደሚሰጥ ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው “እ.ኤ.አ በመጋቢት ወር 2020 በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የአየር መንገዱ የሲንጋፖር በረራ በመከፈቱ ደስተኛ ነን” ብለዋል።
በረራው አየር መንገዱ በእስራ ያለውን ተደራሽነት እንዲሁም በአፍሪካ እና ሲንጋፖር መካከል ጉዞ ለሚያደርጉ ተጓዦች የአየር ትስስርን እንደሚያሰፋ ገልጸዋል።
በአፍሪካ እና ሲንጋፖር መካከል በንግድ፣ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማሳደግ ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
አየር መንገዱ በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር አዳዲስ የበረራ መስመሮችን ለመክፈት ማቀዱንም ነው አቶ መስፍን ያስረዱት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ130 በላይ ዓለም አቀፍ የመንገደኞች እና የካርጎ መዳረሻዎች እንዳሉት በመግለጫው አመልክቷል።