ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምርቶች በቻይና ገበያ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ--በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 1/2015 የኢትዮጵያ ምርቶች በቻይና ገበያ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሺን ቺንሚን ገለጹ።

ቻይና ከየካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን 8 ሺህ 804 የኢትዮጵያ ምርቶች ወደ ቻይና ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ  ፍቃድ  መስጠቷ  ይታወሳል።

ፈቃዱ ቻይና በቅርቡ ይፋ ባደረገችው “የአፍሪካ ልዩ ቀረጥ ማሻሻያ” ማዕቀፍ ስር የሚተገበርና 98 በመቶ የኢትዮጵያ ምርቶች ላይ ቀረጥ እንዲነሳ የሚያደርግ ነው።

በኢትዮጵያ የቻይና ምክትል አምባሳደር ሺን ቺንሚን ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያና ቻይና በተለያዩ  ዘርፎች ያላቸው ትብብር ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል።

በቅርቡ ቻይና ለኢትዮጵያ  የሰጠችው ከቀረጥ ነጻ እድልም አጋርነቱን የሚያጠናክርና የቻይናን ገበያ ለኢትዮጵያ ምርቶች የበለጠ ክፍት የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በቻይና ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዳላቸውና ውሳኔውም ይህንን ፍላጎት የሚመልስና የገበያ ተደራሽነቱን የሚያሰፋ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የሁለቱን አገራት የጋራ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ያለውን የትብብር አድማስ እንደሚያሰፋው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

ኤምባሲው በቀጣይ የኢትዮጵያ ምርቶች በቻይና ገበያ ያላቸውን ተደራሽነት ለማስፋት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ቻይና በኢትዮጵያ የሚካሄዱ በርካታ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ ያላትን አጋርነት በተግባር ማረጋገጧን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ  አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1970 የተጀመረ ሲሆን አሁን ላይ ግንኙነቱ በተለያዩ  የትብብር መስኮች እየተጠናከረ መጥቷል።  

በቅርቡም የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ወደ ቻይና በማቅናት ግንኙነቱ ሊጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ  የቻይና  የስራ ሀላፊዎች ጋር መምከራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም