ቀጥታ፡

የበልግ ዝናብን በተገቢው መልኩ በመጠቀም የግብርና እንቅስቃሴን ማፋጠን ይገባል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት 

አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 1/2015 በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየጣለ ያለውን ወቅቱን የጠበቀ የበልግ ዝናብ በተገቢው መልኩ በመጠቀም የግብርና እንቅስቃሴን ማፋጠን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ። 

የኢንስቲትዩቱ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና ትንበያ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ እንደገለጹት በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ወቅቱን የጠበቀ የበልግ ዝናብ እያገኙ ነው።

ይሁን እንጂ ጥቂት በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የበልግ ዝናቡ መዘግየት እንደነበር አስረድተዋል።

ያም ሆኖ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በአገሪቱ ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች በምስራቅ አማራ፣ የተወሰኑ የደቡብ  ደጋማ አካባቢዎች እንዲሁም የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ ለመፈጠር አመቺ የሆኑ የአየር  ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል። 

በተጨማሪም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተስፋፋና የተጠናከረ የዳመና ክምችትና ሽፋን በመፈጠሩ  በጥቂት የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ደግሞ ከባድ ዝናብ እንድነበር አንስተዋል።

በዚህም የምስራቅ የአገሪቱ ክልል፤ ሐረርና ድሬዳዋ፣ ሰሜን ሶማሌ የደቡብ ደጋማ አካባቢዎች እንዲሁም ምዕራብ ኢትዮጵያ ከቀላል እስከ ከባድ ዝናብ መከሰቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ የግብርና እንቅስቃሴን ለማሳለጥ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።  

እየጣለ ያለው ዝናብ በተለይም "የእርሻ ማሳ ከማዘጋጀት አኳያ የበልግ የግብርና ሥራ እንቅስቃሴዎችን ከማከናወን አኳያ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል" ብለዋል። 

በአንጻሩ የሚጥለው ዝናብ የአየር መለዋወጥ የሚያስከትል በመሆኑ በሰውና በእንስሳት ላይ መጠነኛ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

በተለይም የውሃ አካላት ብክለት እንዳያስከትል የሚጥለውን ዝናብ አዎንታዊ ሁኔታ በመጠቀም ለግብርና  እንዲሁም ለተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።  

የአየር ሁኔታውን ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ የአካባቢ ጽዳት ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በቀጣይ የበልግ ወራቶች ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ዝናብ የሚያስከትሉ የደመና ክምችቶች እየተፈጠሩ መሆናቸውን የአየር ትንበያን ጠቅሰው አብራርተዋል።    

የበልግ የዝናብ ወቅት ከየካቲት 1 እስከ ግንቦት 30 ያሉትን ወራቶች ያጠቃልላል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም