በፍትህ ዘርፍ ያሉ ችግሮች ለመፍታት በቅንጅትና በሙሉ አቅም መስራት ያስፈልጋል-ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ - ኢዜአ አማርኛ
በፍትህ ዘርፍ ያሉ ችግሮች ለመፍታት በቅንጅትና በሙሉ አቅም መስራት ያስፈልጋል-ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ

አዳማ (ኢዜአ) መጋቢት 1/2015 በፍትህ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት በቅንጅትና በሙሉ አቅም መስራት እንደሚያስፈልግ የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ገለጹ።
የፍትህ ሚኒስቴርና የክልል ፍትህ ቢሮዎች የመጀመሪያውን ስድስት ወራት ስራ አፈፃፀም ላይ ያተኮረ የጋራ መድረክ በአዳማ ከተማ እያካሄዱ ነው።
የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለፁት፣ በፍትህ ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችንና የህዝብ ቅሬታዎችን ፈቶ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት በሙሉ አቅም መስራት ያስፈልጋል።
በተለይ ሀገራዊ የፍትህ ስርዓቱን ስኬታማ በማድረግ በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በፌደራልና በክልሎች መካከል የተቀናጀ ትብብርና ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
በመድረኩ በመረጃ አደረጃጀት፣ በሀገራዊ የፍትህ ዘርፍ ሽግግር፣ በማህበረሰብ አቀፍ የፍታብሔር ህጎች እና በግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ላይ ትኩረት ተደርጎ ይመክራል ሲሉም ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አቶ ጉዮ ዋሪዮ በበኩላቸው "በክልሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን በማዘጋጀት ህብረተሰቡ የተሻለ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ እየሰራን ነው" ብለዋል።
በተለይ በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ትኩረት መደረጉንም አመልክተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በፌዴራልና በክልሎች ከቀረቡት 99ሺህ 200 የክስ መዛግብቶች ውስጥ 59ሺህ ለሚሆኑት ውሳኔዎች መሰጠቱን የገለጹት ደግሞ በመድረኩ የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የዕቅድ ዝግጅት ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ መንግስቴ ናቸው።
አቶ መንግስቴ እንዳሉት በተለያዩ መንገዶች የተመዘበረን የመንግሥት ሀብትና ንብረት ከማስመለስ አንፃር በፍትህ ሚኒስቴር ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለስ ተችሏል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ሐረር እና ጋምቤላ ክልሎች 308 ሚሊዮን ብር ማስመለስ የተቻለ ሲሆን፣ ከ80ሺህ 600 በላይ ካሬ ሜትር ቦታ መታገዱንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
"በክልሎች እና በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ መሻሻሎች አሉ" ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት አረጋውያን፣ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አቅመ ደካሞች እና ጠበቃ አቁመው መከራከር የማይችሉ ግለሰቦችን ጨምሮ ከ16ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ነፃ የሕግ አገልግሎት መሰጠቱም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
የተመዘበረን የመንግስት ሀብት ማስመለስ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ፈጣንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፍትህ አገልግሎት መስጠት እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር አሁንም በፌዴራልና በክልል ፍትህ ሴክተሮች ትኩረት የሚሹ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።