ኢንስቲትዩቶቹ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቶቹ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 01/2015 የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጉታ ለገሰ፣ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደጀኔ ሀይለማርያምና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አለሙ ዲሳሳ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የማዕድን ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በሚደረጉ ምርምሮች፣ በሰው ሃይል ልማትና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ነው ተብሏል።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አለሙ ዲሳሳ ስምምነቱ ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር፣ በቴክኖሎጂና በሰው ሀይል አቅም ግንባታ ላይ ከተቋማቱ ጋር በትብብር ለመስራት እንደሚያስችለው አብራርተዋል።
በተመሳሳይ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ጋር አብሮ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጉታ ለገሰ በበኩላቸው የተፈረመው ስምምነት የማዕድን ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚካሔዱ ተግባራትን በቴክኖሎጂና በሰው ሃይል ልማት ለመደገፍ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ጥናትና ምርምሮችን በማድረግም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት በማዕድን ላብራቶሪና በሌሎች አገልግሎቶች ላይ የማዕድን ዘርፉን እየደገፈ እንደሆነ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።