በዓለም የበይነ መረብ አስተዳደር የዲጂታል ክፍፍል የታዳጊ ሀገራት ፈተና በመሆኑ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ኢትዮጵያ አሳሰበች - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም የበይነ መረብ አስተዳደር የዲጂታል ክፍፍል የታዳጊ ሀገራት ፈተና በመሆኑ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ኢትዮጵያ አሳሰበች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 1/2015 በዓለም የበይነ መረብ አስተዳደር የዲጂታል ክፍፍል የታዳጊ ሀገራት ፈተና በመሆኑ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ኢትዮጵያ አሳሰበች።
ኢትዮጵያ ተሳታፊ የሆነችበት የዓለም አቀፉ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ የከፍተኛ መሪዎችና የባለ ብዙ ባለድርሻ አካላት አማካሪ ቡድን በኦስትሪያ ቬየና እየመከረ ነው።
የመድረኩ አባል እና የኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ፣ የዲጂታል ክፍፍል የታዳጊ ሀገራት ፈተና በመሆኑ የጉባኤው አንድ አጀንዳ ሆኖ ምክክር ሊደረግበት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው በማንሳት በአጀንዳነት እንዲያዝ ጠይቀዋል።
ጉባኤውም ይህንኑ ተቀብሎ የዲጂታል ክፍፍል የ2023 ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ አንዱ የመወያያ አጀንዳ ሆኗል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ፣ በታዳጊ ሀገራት በፆታ፣ በቋንቋ፣ በዲጂታል ክህሎት፣ በኢንተርኔት ተደራሽነት፣ በአካባቢ፣ በአይሲቲ እቃዎች እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ገደቦችና ክፍፍሎች እንደሚታዩ ጠቁመዋል።
በዚህም ምክንያት ጉባኤው በዝርዝር መክሮ የመፍትሄ ሃሳቦች ሊያቀርብ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የከፍተኛ መሪዎች መድረኩ ዋና ሰብሳቢ ቪንት ሰርፍ፣ የበይነ-መረብ ደህነት የተጠበቀ፣ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና ፍትሃዊ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
መድረኩም የዲጂታል ክፍፍልን እንደ አንድ አጀንዳ አድርጎ ሊመክርበት ወስኗል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ ባስተናገደችውና በአዲስ አበባ በተካሄደው 17ኛው የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ በመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ የኢትዮጵያን የአይሲቲ እና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በማጉላት ፎረሙ “ተጨባጭ እና ተግባራዊ” ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን እንዲያዘጋጅ መጠየቃቸው ይታወሳል።
18ኛው የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ በቀጣይ ዓመት በጃፓን ይካሄዳል።