በሐዋሳ ከተማ ከ324 ሚሊዮን ብር በላይ ማስፋፊያ ግንባታ የተደረገለት ቡሹሉ የእናቶች እና ሕጻናት ልዩ የሕክምና ማዕከል ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በሐዋሳ ከተማ ከ324 ሚሊዮን ብር በላይ ማስፋፊያ ግንባታ የተደረገለት ቡሹሉ የእናቶች እና ሕጻናት ልዩ የሕክምና ማዕከል ተመረቀ
ሐዋሳ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015 ከ324 ሚሊዮን ብር በላይ ማስፋፊያ ግንባታ የተደረገለት የቡሹሉ የእናቶች እና ሕጻናት ልዩ የሕክምና ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።
የግንባታው ወጪ የተሸፈነው በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሆኑ ተገልጿል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳስ ዘ ካቶሊካዊያን እና የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ማዕከሉን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጤናው ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ብፁዕ ካርዲናሉ ገልጸዋል።
የቡሹሉ የእናቶች እና ሕጻናት ልዩ የሕክምና ማዕከልም ከ44 ዓመታት በፊት ባልተደራጀ ሁኔታ የጤና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ እ.ኤ.አ በ1979 በጤና ጣቢያ ደረጃ ሕክምና መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
ማዕከሉ በሆስፒታል ደረጃ በሚሰጠው አገልግሎት በርካታ እናቶች እና ሕጻናት የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ለማዕከሉ እድገት የክልሉ መንግስት ድጋፍ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
የማስፋፊያ ግንባታው የእናቶችንና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ነው ብፁዕ ካርዲናሉ የተናገሩት።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው "የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከሃይማኖት አስተምሮ በተጨማሪ በጤና፣ በትምህርት እና ማህበራዊ ዘርፎች የምታከናዉነው ተግባር የሚደነቅ ነው" ብለዋል፡፡
በተለምዶ ሎቄ ተብሎ የሚታወቀውና በጤና ጣቢያ ደረጃ አገልግሎቱን የጀመረው የሕክምና ማዕከሉ አሁን ላይ የላቀ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉ የሚያስመስግን እንደሆነ ተናግረዋል።
ማዕከሉ የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የቡሹሉ እናቶች እና ሕጻናት ልዩ ሕክምና ማዕከል በሐዋሳ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስር ከሚገኙ 13 የጤና ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡