ቀጥታ፡

መጤ አረም እና ወራሪ እጽዋትን ለታዳሽ ሀይል አቅርቦት አማራጭነት ለማዋል በርካታ የምርምር ስራዎች እየተሰሩ ነው-ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሴ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015 መጤ አረም እና ወራሪ እጽዋትን ለታዳሽ ሀይል አቅርቦት አማራጭነት እና ለአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት ለማዋል በርካታ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒውቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ የኬምስትሪ መምህር ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ወርሀዊ የገለጻና የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

ውይይቱ እንቦጭና ሌሎች ወራሪ እጽዋት ለታዳሽ ሀይል እና የአካባቢ ጥበቃ ቴክኖሎጂዎች ያላቸው ፋይዳ  በኤሌክትሮ ኬሚስት እይታ በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሀንስ አካዳሚው በበርካታ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በየወሩ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የዛሬው መድረክም ከዚህ ቀደም እንደነበሩት መድረኮች ሁሉ በምሁራን በሚቀርቡ ሀሳቦች ላይ ሀሳብ ለመለዋወጥ ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

የውይይቱ ጽሁፍ አቅራቢ ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሴ የእንቦጭ መጤ ወራሪ እጽዋት ከደቡብ አሜሪካ ተነስቶ 50 በላይ ወደሚሆኑ አገሮች የተስፋፋ አደገኛ አረም መሆኑን ገልጸዋል።

7 የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ ላይ ያመጣው ተጽእኖ 20 እስከ 50 ሚልየን ዶላር እንደሆነም ይገመታል ብለዋል።

ይህ መጤ አረም ለሀይል አቅርቦት፣ በካይ ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድ እንዲሁም እንደ ኢታኖል ሀይድሮጅን እና ሚቴን የመሳሰሉ ኬሚካሎችን ለማምረት ያግዛል ብለዋል።


 

ሌላኛው መጤ አረም በሳይንሳዊ ስሙ ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ /ደርጊሀራ በአፋርኛ/ የተሰኘው መጤ እጽዋት መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም ሰፊ የግጦሽ፣ የእርሻ እና የመኖሪያ ቦታዎችን የወረረ እና የመስኖ የመተላለፊያ መንገዶችን ከጥቅም ውጭ ያደረገ መጤ እጽዋት መሆኑን አስረድተዋል።


 

እነዚህን መጤ እጽዋቶች ወደ ታዳሽ ሀይል ምንጭነት ለመቀየር በርካታ የምርምር ስራዎች እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የጸሀያዊ ህዋስ ዋጋ ታዳሽ ካልሆኑ የሀይል ምንጮች ዋጋ ጋር እየተቀራረበ መምጣቱንም ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።

በነዚህ እጽዋቶች ውስጥ 15 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ሊግኒን የተሰኘውና ለሀይል የሚያገለግል ሞለኪዩል መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም አካባቢን የሚበክሉ ንጥረ ነገሮችን ምንነት እና መጠን የመከታተል ስራዎችም እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

መጤ እጽዋት ለሀይል ማጠራቀሚያና ለአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት ማዋል ስለሚቻል እጹ የሚያደርገውን መስፋፋት መግታት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እና የመንግስት ድጋፍ ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም