በፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ እና አርባ ምንጭ ነጥብ ተጋርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ እና አርባ ምንጭ ነጥብ ተጋርተዋል
አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 30/2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት መርሐግብር የመጨረሻ ወልቂጤ ከተማ እና አርባ ምንጭ ከተማ ሁለት እኩል ተለያይተዋል።
በድሬዳዋ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ጌታነህ ከበደ እና አቤል ነጋሽ ለወልቂጤ ከተማ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
አህመድ ሁሴንና ኬንያዊው ኤሪክ ካፖይቶ ለአርባ ምንጭ ከተማ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን ወደ 21 በማሳደግ ከነበረበት 12ኛ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።
በአንጻሩ አርባ ምንጭ ከተማ በ18 ነጥብ በነበረበት 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ መካሄድ የነበረበት የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ቢሆንም በድሬዳዋ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ሜዳው በመበላሸቱ ጨዋታው ዛሬ እንዲካሄድ የውድድር እና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ መወሰኑ ይታወቃል።