በደቡብ ወሎ ዞን አመርቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ መከናወኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን አመርቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ መከናወኑ ተገለጸ

ደሴ፣ የካቲት 30 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን እየተካሄደ ባለው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ከ46 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መከናወኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት፣ ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ መገርሳ ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ አማራጭ ሳይሆን በዘለቄታ በሕይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡
በመሆኑም በዘንድሮው የበጋ ወራት በተመረጡ 1 ሺህ 398 ተፋሰሶች ላይ ህዝብን በነቂስ በማሳተፍ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ዘንድሮ በጥር ወር አጋማሽ ሲጀመር 44 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም በተደረገው ርብርብ እስካሁን ከዕቅዱ በላይ በማሳካት አመርቂ ስራ ሊሰራ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚሁ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራ ከ500 ሺህ ሰው በላይ እየተሳተፈ መሆኑን ጠቁዋል።
የተደረገው ቅድመ ዝግጅትና የአርሶ አደሩ ቁርጠኝነት ከዕቅድ በላይ ለማከናወን ማስቻሉን ጠቅሰው፤ ስራው ለተወሰነ ጊዜ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
በዞኑ ቀደም ሲል በተሰራው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ምርታማነት ጨምሯል፣ የአፈር ለምነትም ተጠብቋል፣ አርሶ አደሩም ጥቅሙን ተገንዝቦ በራሱ ተነሳሽነት እየሰራና ነባሮቹን እየጠገነ ነው ብለዋል።
የደሴ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መውደድ አማን በበኩላቸው የልማቱን ጠቀሜታ በተግባር በማየታችን በራሳችን ተነሳሽነት ልማቱን በየዓመቱ እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በሰራነው ልማት ምርታማነታችን ጨምሯል፣ ለከብቶቻችን በቂ መኖ ማግኘት ችለናል፣ የተራቆቱ አካባቢዎችም ሲያገግሙ በተግባር በማየታችን ዘንድሮም ተግተን የልማት ስራውን እያከናወን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
የማሳና የተራራ ላይ እርከኖችንና ክትሮችን በመስራት አፈርን ከመሸርሸር መታደግ ከአርሶ አደሩ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን በመረዳት በርብርብ እየሰሩ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ዚነት ሙሳ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል ጥቅሙን በውል ባለማወቃችን ማሳ አጣበበ በሚል ቀን የተሰራውን ሌሊት ያፈርሱ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ጥቅሙን በመገንዘባችን ማፍረስ ቀርቶ በተራ እየጠበቅን ከእንሰሳት ንክኪም ነጻ ማድረግ ችለናል ብለዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ዓመት ከ41 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መከናወኑን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።