የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓም ወደ ካራቺ በረራ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓም ወደ ካራቺ በረራ ይጀምራል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመጨው ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ጀምሮ ወደ ፓኪስታን ካራቺ ከተማ በረራ እንደሚጀምር ተገለጸ።
በረራው በሳምንት ለአራት ቀናት እንደሚደረግም ተጠቅሷል።
አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ወደ ካራቺ ለሁለት የተለያየ ግዜያት በረራ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በረራው ከፈረንጆቹ 2004 ጀምሮ ተቋርጦ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ቀጥታ በረራ ወደ ከተማው በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በርካታ ህዝብ ያላት ካራቺ ለፓኪስታን እና ለተቀረው ደቡብ እስያ አከባቢዎች ወሳኝ መግቢያ እንደምትሆንም ገልጸዋል።
የአየር መንገዱ በረራ ፓኪስታንን ከአፍሪካ ጋር የሚያገናኝ ብቸኛ በረራ መሆኑን ጠቅሰው በአፍሪካ እና በእስያ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በተጨማሪም በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ እየጨመረ የመጣውን የፓኪስታን ኢንቨስተሮችና ጎብኚዎች ቁጥር ከአየር መንገዱ ጋር የሚያስተሳስር ይሆናል ብለዋል።
አየር መንገዱ ወደ ካራቺ የሚያደርገው በረራ በኢሲያ 37ተኛው መዳረሻው መሆኑም ተመላክቷል።
አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም ወደ ፓኪስታኗ ኢስላማባድ በረራ መጀመሩ ይታወቃል።