የአሁኑ ትውልድ ጠንክሮ በመማር የአገሪቱ ዕድገት እንዲፋጠን የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል - አቶ አባዱላ ገመዳ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015 የአሁኑ ትውልድ ጠንክሮ በመማር የአገሪቱ ዕድገት እንዲፋጠን የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ ተናገሩ።


 

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ 12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የዩኒቨርሲቲው ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ተማሪዎች ዕውቅናና ሽልማት አበረከተ።

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ በዩኒቨርሲቲው ሥር የሚተዳደር ትምህርት ቤት ሲሆን 12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ሁሉም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አስመዝግበዋል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።


 

በዚህም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የታብሌት ኮምፒውተር እንዲሁም ለሁለት ተማሪዎች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አባዱላ ገመዳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮ በመውሰድ ሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአቅራቢያቸው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በማገዝ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

ያደገችና የበለጸገች አገር ለመገንባት የአሁኑ ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ተሸላሚ ተማሪዎች ይበልጥ ጠንክረው ትምህርታቸውን መከታተል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የመጣው ውጤት በተማሪዎች ጥረት፣ በመምህራንና በወላጆች ድጋፍ በጋራ የመጣ በመሆኑ በቀጣይም ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።


 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው፤ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ካስመዘገቡ የካምፓሱ ተማሪዎች መካከል 16 600 በላይ ውጤት እንዳስመዘገቡ ጠቅሰዋል። 

ይህም በትብብር ከሰራን በሁሉም መስክ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ያመላክታል ነው ያሉት።

በተማሪዎች ላይ ከሰራን ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ ውጤት በመሆኑ በቀጣይም ከዚህ በበለጠ ሁኔታ እንሰራለን ብለዋል።


 

ሽልማት የተሰጣቸው ተማሪዎች በበኩላቸው፤ በቀጣይ የከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ጠንክሮ በመመራመር ለአገራቸው ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚወጡ ገልጸዋል።


 

የተሰጣቸው ሽልማትም ለቀጣይ የትምህርት ሂደት ትልቅ ሞራል እንደሆናቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም