ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የዩኒቨርሲቲው ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ተማሪዎች ሽልማት አበረከተ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015 ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ 12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የዩኒቨርሲቲው ሳይንስ ርድ ካምፓስ ተማሪዎች ዕውቅናና ሽልማት አበረከተ።

ቀዳማቂ ምኒሊክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ በዩኒቨርሲቲው ስር የሚተዳደር ትምህርት ቤት ሲሆን፤ 12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ሁሉም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡


 

በዛሬው እለት ደግሞ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና፣ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አባዱላ ገመዳ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በዚህም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡት ተማሪዎች የታብሌት ኮምፒውተር እንዲሁም ለሁለት ተማሪዎች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡


 

የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ በዚሁ ወቅት እንደ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሁሉ ሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአቅራቢያቸው የሚገኙ ትህምርት ቤቶችን በማገዝ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአደገችና የበለጸገች አገር ለመገምባት የአሁኑ ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ  ተሸላሚ ተማሪዎች ይበልጥ ጠንክረው ትምህርታቸውን መከታተል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ካስመዘገቡ የካምፓሱ ተማሪዎች መካከል 16 ከስድስት መቶ በላይ ውጤት እንዳስመዘገቡ ጠቅሰዋል፡፡

ይህም በትብብር ከሰራን በሁሉም መስክ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደምንችል ያመላክታል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም