በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የእምነት ተቋማት ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የእምነት ተቋማት ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ምሁራን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015 በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ የእምነት ተቋማት የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።
ምሁራኑ ለኢዜአ እንደገለጹት በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ የእምነት ተቋማት በየደረጃው የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
በኬንያ ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍናና ሃይማኖት ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሐሰን ኦማሪ እንደገለጹት፤ የሃይማኖት ተቋማት ሰላምና አንድነትን ለማምጣት ሚናቸው ከፍተኛ ነው።
አፍሪካ የእምነት ተቋማት በስፋት የሚገኝባት ቢሆንም በእርስ በርስ ግጭት፣ ጦርነትና መገዳደል ምክንያት የሰላምና አንድነት እጦት በስፋት የሚስተዋልባት አህጉር መሆኗን አንስተዋል።
በመሆኑም ተቋማቱ ተከታዮቻቸውን ፍቅር፣ ትህትናን፣ መከባበርና መተሳሰብን በመስበክ ለሰላምና አንድነት ዘብ የሚቆም ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ርብርብ ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት በአህጉር ደረጃ ዘላቂ ሰላምና አንድነትን በማምጣት የማኅበረሰብና ምጣኔ ኃብት ውህደት ለመፍጠር በመንግሥታት የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍ ሚናቸው የላቀ ነው ብለዋል።
በናይጄሪያ ሌጎስ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ሃይማኖት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ፕሮፌሰር አኪን ቢዳፖ ኢቢ የሃይማኖት ተቋማት ሥነ-ምግባርን የሚያስተምሩ ከመሆናቸው አንጻር የእርስ በእርስ ግንኙነትና መከባበርን ለማጠናከር የበለጠ መሥራት ይገባል ብለዋል።
የእርስ በርስ ግጭት የሚበዛባት አፍሪካ ግጭትን ቀድሞ በመከላከልና ከተከሰተ በኋላ ሰላም በማምጣት የሃይማኖት ተቋማት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መምህር የሆኑት አባ አብነት አበበ በዓለም፣ በአህጉርና በአገር ደረጃ የእርስ በርስ ግጭትና የሰላም እጦት እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለግጭት መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን በመነጋገር መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል ትምህርቶችን እየሰጠች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
በአህጉሪቷ በሚገኙ የእምነት ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከርና በሰላም ጉዳይ ላይ ያለውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም ምሁራኑ ጠቁመዋል።