በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በለሙ ተፋሰሶች 1ሺህ 600 ዜጎችን በንብ ማነብ ሥራ ለማሰማራት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በለሙ ተፋሰሶች 1ሺህ 600 ዜጎችን በንብ ማነብ ሥራ ለማሰማራት እየተሰራ ነው
ሐረር ፤ (ኢዜአ) የካቲት 29/2015 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በለሙ ተፋሰሶች ላይ 1ሺህ 600 ዜጎችን በንብ ማነብ ሥራ ለማሰማራት ዘመናዊ የንብ ቀፎ እያሰራጨ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታሁን ንጋቱ እንደገለጹት፣ በዞኑ በተከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ ምንጮች ከመጎልበታቸው ባለፈ ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎችም ወደ አረንጓዴነት ተቀይረዋል።
የለሙ ተፋሰሶች ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠራቸው የተደራጁ ዜጎችን በንብ ማነብ ሥራ እንዲሰማሩ ዘመናዊ የንብ ቀፎ የማሰራጨት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
አቶ ጌታሁን እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በማህበር ለተደራጁ 1ሺህ 600 ወጣቶች 2ሺህ 500 ዘመናዊ የንብ ቀፎ እየተሰራጨ ይገኛል።
እንደ አቶ ጌታሁን ገለጻ በዞኑ በማር ምርት፣ በዶሮ እና ከብት እርባታ፣ በጓሮ አትክልትና ሌሎች የሌማት ቱሩፋት ሥራዎች ላይ ዜጎች የተቀናጀ ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው።
የፈዲስ ወረዳ አየር ንብረት ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ በመሆኑ በወረዳው ከፍተኛ ማር እንደሚመረት የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቸሩ ቀነኒ ናቸው።
ከወረዳው የሚገኘውን የማር ምርት ወደ ድሬዳዋ፣ ሐረር እና ጅግጅጋ ከተሞች በመላክ አርሶ አደሩ የተሻለ ገቢ እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በወረዳው በለሙ ተፋሰሶች ላይ በማህበር ተደራጅተው ለሚሰማሩ 150 ወጣቶች 200 ዘመናዊ የንብ ቀፎ መሰራጨቱንም ገልጸዋል።
ዘመናዊ የንብ ቀፎ ድጋፍ ከተደረገላቸው የፈዲስ ወረዳ ኢዶ ባሰ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሂንዲያ አህመድ እንደሚገልጹት፣ በባህላዊ መንገድ ስናመርት የነበረውን ማር በዘመናዊ ሁኔታ በተሻለ ለማምረት የቀፎው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት የተሻለ የማር ምርት ለማግኘት እድል እንደሚፈጥርላቸውም ተናግረዋል።
"በለሙ ተፋሰሶች ጠንክረን ከሰራን ውጤታማ እንሆናለን" ያለው ደግሞ በእዚሁ ወረዳ ኡመርኩሌ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አዲል መሀመድ፣በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት አቅደው ወደሥራ መግባታቸውን ገልጿል።
"አሁን የተሰጠን ዘመናዊ የንብ ቀፎ ከባህላዊው ቀፎ አንጻር የተሻለ ምርት እንደሚያስገኝ በተለያዩ አካባቢዎች ተመልክቻለሁ" ያሉት ደግሞ ከፊል አርሶ አደር ሀሰን ጁጌ ናቸው።
ዘመናዊ የንብ ቀፎውን በመጠቀም ከበፊቱ የተሻለ የማር ምርት ለማግኘት ጠንክረው እንደሚሰሩ አያይዘው ተናግረዋል።