የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ድርጅት በደቡብ ኦሞ ድርቅ ላጋጠማቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ድርጅት በደቡብ ኦሞ ድርቅ ላጋጠማቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ
ጂንካ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015 የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ድርጅት በደቡብ ኦሞ ዞን ድርቅ ላጋጠማቸው የማህበረሰብ ክፍሎች 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው 450 ኩንታል የምግብ ዱቄት ድጋፍ አደረገ።
የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አቅናው ካውዛ ድጋፉን ለዞኑ አስተዳደር ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት ድርጅቱ በድርቅ የተጎዱ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ ነው።
የስንዴና የበቆሎ ዱቄት ያካተተው ድጋፍ ከ3ሺህ በላይ ለሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሆን መሆኑን አስታውቀዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ አቶ መሠለ መስፍን የድርቁን አደጋ ለመታደግ ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ለተጎጂዎች በፍጥነት እንደሚከፋፈል አረጋግጠዋል።
የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዱባ ያራ በበኩላቸው በዞኑ የተከሰተው የድርቅ አደጋ እየሰፋ በመምጣቱ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው አመልክተዋል።
በደቡብ ኦሞ ዞን ለአራት ተከታታይ ዓመታት የዘለቀው ድርቅ በርካታ ዜጎችን ለምግብ እጥረት እንዳጋለጠና የቤት እንስሳትም በድርቁ ሳቢያ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ጠቁመዋል።