ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እያከናወነ ያለው ስራ የሚደነቅ ነው-የፓኪስታን ባለኃብቶች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015 የኢትዮጵያ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እያከናወነ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙ የፓኪስታን ባለኃብቶች ተናገሩ።

ኢትዮጵያና ፓኪስታን በኢኮኖሚና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ከፍተዋል።   

ከስድስት ወራት በፊት ኢትዮጵያ በፓኪስታን ኤምባሲዋን የከፈተች ሲሆን፤ በዚህም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

ኤምባሲው ባመቻቸው መሰረት 71 አባላት ያሉት የፓኪስታን የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ ከየካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጨችን በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችና ምቹ ሁኔታዎችን በሚመለከት ለልዑኩ ገለጻ ተደርጓል፡፡

የልዑኩ አባላት የቦሌ ለሚና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የጎበኙ ሲሆን በፓርኮቹ ውስጥ ከተሰማሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉ የፓኪስታን ባለኃብቶች እንደተናገሩት፤ በጉብኝቱ ያዩት የኢንቨስትመንት አማራጮች ሳቢ ናቸው።

መንግሥት ኢንቨስትመንት ለመሳብ እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረትም አድንቀዋል።


 

ከልዑካኑ አባላት መካከል ኢብራሂም ካሊድ ታዋብ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ መንግሥት ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ያወጣቸው ፖሊሲዎችና አሰራሮች ኢንቨስትመንት የመሳብ ትልቅ አቅም አላቸው ብለዋል። 

ጨርቃጨርቅ፣ መድሃኒት ማምረትና ግንባታ ዘርፍ ኢንቨስት ሊደረግባቸው የሚችልባቸው መስኮች መሆናቸውን ተመልክተናል፤ ሌሎች የፓኪስታን ባለኃብቶችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ ብለዋል።

በተለይም የግንባታው ዘርፍ በኢትዮጵያ በጣም እያደገ መሆኑን ጠቁመው "በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው" ሲሉም ነው የገለጹት። 

የፓኪስታን ጨርቃጨርቅ አምራቾች ማህበር ሊቀ-መንበር ዛሂድ ማዝሃር በበኩላቸው በኢትዮጵያ ቆይታችን ለምንጠይቀው ጥያቄ ሁሉ ፈጣን ምላሽ እያገኘን ነው፤ ይህ ደግሞ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም