ቀጥታ፡

የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ አበረከቱ 

ያቤሎ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015  የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ  በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 18 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ፣ መድኃኒት እና የሕክምና ግብዓት ድጋፍ አደረጉ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ድጋፉን በቦረና ዞን ዱቡልቅ ወረዳ በድርቅ የተጎዱ ወገኖች ማዕከል አስረክበዋል።

ዶክተር ሊያ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከድጋፉ መካከል 10 ሚሊየን ብር የሚሆነው የመድኃኒት፣ አልሚ ምግብና ህክምና ግብዓት መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀሪው የምግብ ዘይትና የእህል ድጋፍ ነው።

ጤና ሚኒስቴር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የሰው ኃይል ከማሰማራት ባለፈ የሕክምና ግብአቶችንና የአልሚ ምግብ  ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን  አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የድርቅ አደጋ በዘላቂነት ለመቅረፍ በተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና በተዋረድ በሚገኙ ተቋማት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን ነው ዶክተር ሊያ የገለጹት።

ችግሩ እስከሚፈታ ድረስ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተያያዘም ዶክተር ሊያ እና የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ድርቁ ባስከተለው ምክንያት ለምግብ እጥረት ተጋልጠው በቦረና ዞን ያቤሎ አጠቃላይ ሆስፒታል የሚገኙ ሕጻናት እና አረጋዊያንን የጎበኙ ሲሆን ሆስፒታሉ እነዚህን ወገኖች ለመታደግ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።


 


 

በቦሬና ዞን ዱቡልቅ ወረዳ በድርቅ የተጎዱ ወገኖች ማዕከል የሚገኙ ዜጎች ድርቁ ባስከተለው አደጋ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት ሕይወታችን ለማቆየት በተለያየ መንገድ ድጋፍ እየተደረገላቸው ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት ሕጻናት እና አረጋዊያን ለምግብ እጥረት እየተጎዱ በመሆናቸው የሚደረገው ድጋፍ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም