ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና የጸጥታ ስጋቶችን በጋራ ለመቆጣጠር ተስማሙ

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 30/2015፦ ኢትዮጵያና ኬንያ በድንበር አካባቢ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችንና ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል ተስማሙ።

የኢትዮ-ኬንያ ድንበር ተሻጋሪ የደህንነት ምክክር ትናንት በናይሮቢ መካሄዱን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራ የልዑካን ቡድን ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች ጋር በተለያዩ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል።

ሁለቱ ወገኖች በጋራ ድንበራቸው ላይ የሚያጋጥሙ የጸጥታ ስጋቶችን በአፋጣኝ ለመፍታትም ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖና የኬንያ ፕሪንሲፓል ሴክሬቴሪ ዶክተር አብርሃም ኮሪር ሲንጎይ በድንበር አካባቢ ያሉ የጸጥታ ስጋቶችን በጋራ ለመመከላከል የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ተገልጿል።

በዚህ መሰረትም ዋና መቀመጫውን ሰሜን ኬኒያ አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ በመሻገር የሽብር ጥቃት የሚፈፅመውን የሸኔ የሽብር ቡድን ለመግታትና ለማስቆም በጋራ እንደሚሰሩ ተስማምተዋል።

በተጨማሪም አልሻባብና የሸኔ ሽብር ቡድን በመተሳሰር እየፈፀሙ ያሉትን የሽብር እንቅስቃሴ ለመዋጋት የሁለቱ ሃገራት የፀጥታ አካላት በድንበር አካባቢ የጋራ ኦፕሬሽን ማካሄድ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም ተስማምተዋል።

በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት በመስራት ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መቆጣጠርና ወንጀለኞችንም ተጠያቂ ማድረግን ጨምሮ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን በጋራ መከላከል በስምምነቱ ውስጥ የተካተተ መሆኑም ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም