በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አርባ ምንጭ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ይጫወታሉ - ኢዜአ አማርኛ
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አርባ ምንጭ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ይጫወታሉ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015 በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር አርባ ምንጭ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ዛሬ 11 ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አርባ ምንጭ ከተማ እስከ አሁን በሊጉ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ አራት ጊዜ በመሸነፍ፤ ስምንት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በ15 ጨዋታዎች 18 ግቦችን ሲያስቆጥር 20 ጎሎች ተቆጥረውበት በ17 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ላይ ተቀምጧል።
አርባ ምንጭ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ሲሆን
አንድ ጊዜ ተሸንፎ፤ ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አምስት ጊዜ ተሸንፎ፤ አምስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በ15 ጨዋታዎች 18 ጎሎችን ሲያስቆጥር 17 ግቦች ተቆጥረውበት በ20 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንድ ሲያሸንፍ፤ ሁለት ጊዜ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ መካሄድ የነበረበት የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ቢሆንም በድሬዳዋ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ሜዳው በመበላሸቱ ጨዋታው ዛሬ እንዲካሄድ የውድድር እና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ መወሰኑ ይታወቃል።
በተያያዘ ዜና ትናንት በተካሄዱ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ ኢትዮ ኤሌትሪክን 3 ለ 1 እንዲሁም አዳማ ከተማ ፋሲል ከነማን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።