ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት እውን እንዲሆን ከፖሊሲ ቀረፃ ጀምሮ ገለልተኝነቱና አሳታፊነቱ ሊጠበቅ ይገባል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 29/2015 በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት እውን እንዲሆን ከፖሊሲ ቀረፃ ጀምሮ ገለልተኝነቱና አሳታፊነቱ ሊጠበቅ እንደሚገባ የመገናኛ ብዙኃን እና ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ተናገሩ።

የፍትሕ ሚኒስቴር በብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ የግብዓት ማሰባሰብ መድረክ ከሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከሚዲያና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ሥራ ቡድን አባል ዶክተር ማርሸት ታደሰ፤ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ፍትሕ ማስፈን፣ እውነቱን መፈለግ፣ ዕርቅ፣ ተበዳዮችን መካስ፣ የእርምት እርምጃ መውሰድ እና ሰብዓዊ በደሎች እንዳይደገሙ የማድረግ ግቦች እንዳሉት ገልጸዋል።


 

ባለፉት ዘመናት የተፈጸሙ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመደበኛው ሕግ ሥርዓት ለማስተናገድ ሲያዳግት የሚተገበር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት የተደረጉ የሽግግር ፍትሕ ተሞክሮዎች በሕግ ማዕቀፍ ባለመመራታቸው የተፈለገውን ግብ እንዳላመጡ አስታውሰዋል።

በዚህም በቀጣይ ለታሰበው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ስኬታማ ለማድረግ ማስፈጸሚያ የሕግ ማዕቀፍ ማርቀቅ በማስፈለጉ የፖሊሲ አቅጣጫ ግብዓቶች መሰብሰብ እንደተጀመረ ተናግረዋል።


 

የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ሔኖክ መለሰ በበኩላቸው፤ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ አሳታፊ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

በሽግግር ፍትሕ ተበዳዮች ፍትሕ የሚያገኙበት፣ ዕውነት የሚወጣበት፣ ቁርሾ የሚታከምበት፣ ፖለቲካዊ ችግሮች የሚፈቱበት፣ ሀገራዊ ሰላም እና ዕርቅ ለማምጣት የሚያግዝ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንደ ባለድርሻ አካል ከሽግግር ፍትሕ ሂደት ፖሊሲ ቀረፃ እስከ አፈጻጸሙ ባሉ ሂደቶች ንቁ ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከገለጹ የመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሲቪክ ማኅበረሰብ እና የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር ለተፈጸሙ ግፎች የሽግግር ፍትሕ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ታምራት ኃይሉ እና የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምክትል ፕሬዝዳንት ታደለ ደርሰህ፤ በሂደቱ ገለልተኝነት እና አሳታፊነት ሊጠበቅ እንደሚገባው ገልጸዋል።

በሚዲያ ተቋማት ረገድ በሽግግር ፍትሕ ሂደት ሚናቸው እንዲጠበቅ እና ሥራዎቻቸውንም በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችም የድርሻቸውን እንዲወጡ ምህዳሩ እንዲሰፋ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም