የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተመለከቱት ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ዝግጁ ሆነዋል- በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተመለከቱት ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ዝግጁ ሆነዋል- በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 29/2015 የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተመለከቱት ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ዝግጁ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሾዛብ አባስ ገለጹ፡፡
ከ70 በላይ የፓኪስታን ንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ ለመመልከት ከቀናት በፊት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
ለልዑካን ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በኢትዮጵያ ስላሉት የኢንቨስትመንት አማራጮች በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ገለፃና ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል።
ልዑኩ በትናንትናው ዕለት የቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የጎበኙ ሲሆን ለጨርቃ ጨርቅና ለመድሃኒት ፋብሪካ ዝግጁ የተደረጉ ሼዶችንም ተመልክተዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም የአንድነት ፓርክን የጎበኙ ሲሆን በቀጣይም ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።
የፓኪስታን ባለሃብቶች በሲሚንቶ፣ በግብርና እና የማዕድን ዘርፍን ጨምሮ በሌሎችም መስኮች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸው ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሾዛብ አባስ፤ የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተመለከቱት ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠውን ልዩ ትኩረት በመገንዘብ በዘርፉ በስፋት የመሳተፍ ፍላጎትም እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር፤ የፓኪስታን ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ አገር መሆኗን በአግባቡ ተረድተው በተለያዩ መስኮች የመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል።
በአፍሪካ በሂደት ላይ ያለውን ነጻ የንግድ ቀጣና እንቅስቃሴ በመጠቀም የገበያ አማራጭ እንደሚያገኙ በመረዳት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የማምረቻ ቦታ የጠየቁ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
የፓኪስታን ንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ ቡድን መሪ ኢብራሂም ካሊድ ታዋብ፤ የአንድነት ፓርክ ጉብኝታቸውን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ፓርኩ የኢትዮጵያን ታሪከ የያዘ እና ድንቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ኢንቨስት ከማድረግ ባለፈ ያሏትን እምቅ ሃብቶችና ማራኪ ስፍራዎች ለማወቅ መቻላቸውን ገልጸዋል።
የፓኪስታን ንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ በዛሬው ውሏቸው ከአንድነት ፓርክ ባለፈ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየምን ጎብኝተዋል፡፡