መንግስት ለሆርቲካልቸር ዘርፍ ምቹ ከባቢ የሚፈጥር የፖሊሲ እና አሰራር ማሻሻያ እንዲያደርግ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለሆርቲካልቸር ዘርፍ ምቹ ከባቢ የሚፈጥር የፖሊሲ እና አሰራር ማሻሻያ እንዲያደርግ ተጠየቀ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 29/2015 መንግስት በሆርቲካልቸር ዘርፍ ምቹ ከባቢ መፍጠር የሚያስችል የፖሊሲ እና የአሰራር ማሻሻያ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማህበር ጠየቀ።
ስምንተኛው “ሆርቲፍሎራ ኤክስፖ” የተሰኘው ዓለም አቀፍ የአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ኤክስፖ ዛሬ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።
የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማህበር የቦርድ ሊቀ-መንበር አቶ ነጋ መኳንንት በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሆርቲካልቸር በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በሕግ ማዕቀፍ ክፍተት፤ በመሬት አቅርቦትና በሰላም እጦት ቢፈተንም ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት ዘርፍ ነው፡፡
ዘርፉ ከፍተኛ የስራ ዕድል በመፍጠርና የሴቶች ተጠቃሚነትን በማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው በመጥቀስ፤ መንግስት የፖሊሲ እና የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ መንግስት የንግድ ስራዎችን የሚያቀላጥፉ ማሻሻያዎች ከሚያደረግባቸው ዘርፎች መካከል ሆርቲካልቸር አንደኛው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከሆርቲካልቸር የሚገኘው ገቢ እያደገ መምጣቱን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሰባት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የዘርፉ ምርቶች ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
ሆርቲካልቸር ለሴቶች የስራ እድል በመፍጠር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ድርሻ እያሳደገ ቢሆንም በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ አሁንም ያልተነኩ ዕድሎችን መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ያሉ እንደሎችን መጠቀም እንደሚገባ በመጠቆም፤ መንግስት ዘርፉ የሚያስፈልገውን አስተዳደራዊ ጉዳዮች ለመፍታት ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ በበረራ አገልግሎቱ የሆርቲካልቸር ዘርፉን በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2021/2022 ከ75 ሺህ ቶን በላይ አበባ ወደ አውሮፓ ገበያ ማጓጓዙንም አመላክተዋል፡፡
የአበባ ምርቶችን የማጓጓዝ አቅሙን ለማሳደግም የእቃ ጫኝ አውሮፕላኖችን መጨመሩንና ወቅቱ የደረሰባቸውን የማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ 89 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል።