የሴቶች አጀንዳ የህዝብ ጉዳይ እንዲሆን የሚሰራ ጠንካራ ማህበር ያስፈልጋል-ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶች አጀንዳ የህዝብ ጉዳይ እንዲሆን የሚሰራ ጠንካራ ማህበር ያስፈልጋል-ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 29/2015 የሴቶች አጀንዳ የሕዝብ ጉዳይ እንዲሆን የሚሰራ እውቀትና ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ለዚህ ዓላማ የሚያስተባብር ጠንካራ ማህበር ያስፈልጋል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አለም አቀፉ የሴቶች ቀንን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የሴቶችን ችግር ለመፍታትና እኩልነትን ለማረጋገጥ ከተበታተነ አካሄድ ይልቅ በጋራ መስራትን ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
በሴቶች ላይ ከሚደርሰው የችግር አዙሪት ለመውጣት ቁልፍ ጉዳይ የሴቶች መደራጀት መሆኑን ገልጸው የመብት ትግል የተናጠል ትግል ስላልሆነ ሴቶች ጠንካራ የጋራ አጀንዳ ሊይዙ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለንን ትስስር ለማጠናከር ከአራት ዓመት በፊት የተመሠረተው "የአፍሪካ ሴት መሪዎች ጥምረት "AWN" የኢትዮጵያ ቅርንጫፍን ማጠናከርና የልምድ ልውውጦችን ማጎልበት ይጠበቅብናል ሲሉም አክለዋል።
"ይህንን የሴቶች ወር በማስመልከት ያለፈውን እንድንገመግም፣ የዛሬውን በርትተን እንድንሠራና የወደፊቱን እንድናቅድ ቆም ብለን ማሰብ ይገባናል" ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የምንገነባት ኢትዮጵያ ሴቶችና ታዳጊ ሴት ልጆች ሴት በመሆናቸው፣ በራሳቸው በመተማመናቸው የማይሸማቀቁባት፣ በአገራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ ተካፋይ የሚሆኑባት፣ ሃሳባቸው የሚሰማባት እንድትሆን ሁላችንም እንትጋ ብለዋል።
የሴቶች ቀን በዓመት አንድ ግዜ ብቻ የሚታወስ ሳይሆን የ365 ቀናት ስራ መሆን አለበት ያሉት ፕሬዝዳንቷ ቀኑ ያለፈውን እየኖርን የወደፊቱን ከሴቶች እኩልነት፣ ተጠቃሚነት እና ከሰው ልጅ መብት አንጻር እንድንቃኝ አስታዋሻችን ነው ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።