ባለፉት 6 ወራት በጭሮ ከተማ ከ3ሺህ 400 በላይ የሆኑ ዜጎች የስራ እድል አግኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት 6 ወራት በጭሮ ከተማ ከ3ሺህ 400 በላይ የሆኑ ዜጎች የስራ እድል አግኝተዋል
ጭሮ (ኢዜአ) የካቲት 29/2015 ባለፉት 6 ወራት ከ3ሺህ 400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የጭሮ ከተማ አስተዳደር የስራ እድልና ክህሎት ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዘሃራ ኢብራሂም ለኢዜአ እንደገለጹት የስራ እድሉ የተፈጠረላቸው 3ሺህ 485 ዜጎች በማህበራት የተደራጁና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ቅጥር ነው።
ከእነዚህ መካከል በ686 የሰው ሃይል የተደራጁ 155 ማህበራት ሲሆኑ፤ 299 በቅጥር እንዲሁም 2 ሺህ 500ዎቹ ደግሞ በመሰረተ ልማትና ሌሎች የመንግስት ፕጀክቶች የስራ እድል ማግኘት ችለዋል፡፡
ወደ ስራ ለተሰማሩ ማህበራትም በሲንቄ ባንክ ድጋፍ ሰጪነት 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የብድር አገልግሎት የተመቻቸላቸው መሆኑን ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
ከገንዘብ ብድር አገልግሎቱ በተጨማሪ ሁለት ማህበራት የሳሙና ማምረቻና የዳቦ መጋገሪያ የመሳሰሉ የማሽን አቅርቦት ማግኘታቸውም ተጠቁሟል፡፡
በተለይም ከውጭ ሀገር የሚመጣውን ምርት በሀገር ውስጥ የመተካት እቅዱን ከግብ ለማድረስና የኑሮ ውድነትን ለማርገብ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ወይዘሮ ዘሃራ አክለዋል፡፡
ወደ ስራ ለተሰማሩት 121 አዳዲስና ነባር ማህበራት የካይዘንና የኢንዱስትሪ አገልግሎት ኤክስቴንሽን ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
28 አዳዲስና 11 የተፈቀደላቸውን የስራ ጊዜ ካጠናቀቁ ማህበራት የተለቀቁ በድምሩ 39 የመስሪያ ቦታዎች /ሼዶች/ በ6 ወራቱ የስራ ጊዜያት ለስራ ፈጣሪዎች መተላለፉንም ጠቅሰዋል፡፡
የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት ወጣቶች መካከል ወጣት ኦሊያድ ጀማል በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ከተመረቁ ሰባት ጓደኞቹ ጋር በመቀናጀት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በሳሙና ማምረት ዘርፍ ላይ መሰማራታቸውን ገልጿል፡፡
በመንግስት በኩል በ2 መቶ 37 ሺህ ብር ዋጋ ያለው የሳሙና ማምረቻ ማሽን 20 በመቶውን ቅድሚያ በመቆጠብ እንዲያገኙ እንደተመቻቸላቸው ተናግሯል፡፡
በተጨማሪም ለስራ ማስኬጃ 670ሺህ ብር ከሲንቄ ባንክ የብድር አገልግሎት ማግኘታቸውን በመጥቀስ።
ደረቅና ፈሳሽ የሳሙና አይነቶችን በማምረት የጀመሩትን ስራ ኮስሞቲክስን ጨምሮ ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ የማሳደግ ራእይ ይዘው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ወጣቱ ተናግሯል፡፡
ወጣት ነኢማ ሀሚድ በበኩሏ በዳቦ መጋገሪያና ማከፋፈያ ዘርፍ ከጓደኞቿ ጋር ተደራጅታ መስራት መጀመሯን ተናግራለች፡፡
መንግስት ባመቻቸላቸው የዱቤ ግዢ መሰረት የተረከቡት 200ሺህ ብር ዋጋ ያለው የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ብድር በመክፈል ላይ መሆናቸውንና አሁን ላይ ከ200ሺህ ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ መያዝ መቻላቸውን አክላለች፡፡
በቀን እስከ ሶስት ኩንታል ዱቄት እንደሚጠቀሙና ከ10ሺህ በላይ ዳቦ እያመረቱ ቢገኙም የዱቄት አቅርቦት ላይ ያለው ችግር ስራው ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረባቸው መሆኑን ገልጻለች፡፡
ወጣት ነኢማ በቀጣይ ስራቸውንና አገልግሎታቸውን ከፍ ለማድረግ ባቀዱት መሰረት በኬክ ምርትና በሌሎች ምርቶች ላይ በመሰማራት በስፋት ለተጠቃሚው ለማቅረብ ማቀዳቸውን አስታውቃለች፡፡