ሴትነት እና እናትነት

2451


(አየለ ያረጋል)
እስኪ መላ ስጪኝ መላ ካንቺ ይገኛል
እኔማ ወንድ ነኝ ይደናገረኛል…
(የማኅበረሰቡ ቃላዊ ግጥም)
 
ሴትነት እናትነትን ለመግለጽ ቀርቶ በጥቂቱ ለመረዳት የ’እናት ልብ’ መታደል የሚሻ ይመስላል። ጥቂት ወንዶች ይህን ጸጋ ይቸራሉ። ልክ እንደ ዶክተር ይሁኔ አየለ። የስነ-ምግብ ሳይንቲስቱ ዶክተር ይሁኔ አየለ ‘እናት’ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ድንቅ መጽሐፍ የሴትነት እና እናትነትን ከፍታ በ’ኩርሽም’ ቃላት ተራቀውበታል። የሴቶች ቀንን (ማርች-8) ሰበብ በማድረግ ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ መታሰቢያነቱ እናትን አስበው በ‘እናትነት’ ቅን ልቦና ‘እናትን’ ላበረከቱልን ዶክተር ይሁኔ አየለ ነው።
 
‘እናት፤ የሴት ልጅ ስንክሳር፤ ከቤተሰባዊ ሕይወት እስከ ሐልዮመንበርት’ በሚል ርዕስ በቅርቡ ባሳተሙት (በ406 ገፆች በተቀነበበ) አርበ ጠባብ መጽሐፍ ሴትነትን ከዘፍጥረት እስከ አሁን ዘመናትን ዋጅተው፣ እናትነትን ከሴትነት ዘንቀው፣ የእናትነት ጸጋን ከነባራዊ ሃቅ ጋር አሰነናስለው፣ የእናትነትን ልዕለ-ተፈጥሮ አርቅቀው፣ የዓለምን ክብር-ነሽነት ከነገረ-ሃይማኖት እስከ ነገረ-ባህልና ፍልስፍና ፈትተው፣ የማኅበረሰቡን ምልከታ ዝንፈት እና ሚዛን ጉድለት ከማኅበራዊ እስከ ፖለቲካዊ መገለጫዎች አዛምደው አቅርበውታል።
ዶክተር ይሁኔ አየለ “እናት” በተሰኘ እናት የሆነ መጽሐፋቸው እናትነትን በልኩ ነጽረውታል። ሴትነት በኢትዮጵያ የአስተሳሰብ ሰለባነቱን፣ ነገረ-ሴትነትን ከንጽረተ-ሴትነት ቃኝተውታል። በእሳቤ ሚዛን ሰለባነት ዓለም ውስጥ ከንግስት ማክዳ እስከ ንግስት ፉራ፣ ከሰብለ ወንጌል እስከ ድል ወንበራ፣ … ብርቱ ኢትዮጵያዊት ሴቶችን ሕይወት ጨልፈውታል። የሴትነትን ጸጋዎች ጨልፈው በሴትነት ላይ የሚፈጸሙ የሀበሻ ግፎችን ተንትነውበታል።
 
ሴቶች የማኅበረሰቡ ግፍ ሰለባዎች፣ የማኅበራዊ ፍትህ ጉድለት ሰለባዎች እንደሆኑ በቅጡ ገልጸውታል። ዳሩ ሴትነት ጀግና እና ብልህ፣ የቤተሰብ መሰረት፣ የደስታና እልልታ እናት፣ ቃል ኪዳንና ክብር ጠባቂ እንደሆነ ገልጸዋል።
“ሴት ልጅ ባለብዙ ጸጋዎች ናት። ከጸጋዎቿ መካከል ጀግንነት እና ብልሃት ይጠቀሳሉ። … ሴት ልጅ ባህልን ፈጥራ የማኅበራዊነትን ማስተሳሰሪያ ገመዶች ገምዳ አስተሳስራ ማኅበረሰብን የተከለች ሥርዓት ናት። … ቤተሰብ የአንድ ማኅበረሰብ የመጀመሪያ ተቋም ነው። የተቋሙ ባለሥልጣን (እመቤት) ሴት ናት። ያቺ ሴት እናት ናት። ቤተሰብ የስብዕና መሰረት የሚባለው እናትን ምሰሶ አድርጎ ነው” (ገጽ-285)
 
ሴት ልጅ መለኛ መሆኗን ማኅበረሰባችን ቢያምንም ሴትነትን ግን እንዳላከበረ አሉታዊ ይትባህልና ኪነተ- ቃሉን ዘይቤ ያወሳሉ። በእርግጥ የእናትን ምቹነት እና ዋጋ ከፋይነት የሚያትቱ የአማርኛ ተረትና ምሳሌዎችም አሉ። ለምሳሌ ዳንኤል አበራ “የአማርኛ ተረትና ምሳሌዎች” በሚለው መጽሐፋቸው “እናት ትረገጣለች እንደመሬት፤ እናት ለልጄ ልጅ ለነገዬ፤ እናቷን አይተህ ልጅቷን አግባ፤ እናት የሌለው ልጅ እንደ ጌሾ፤ ሳይበላ የበላ ሳይናገር ዋሾ…” የሚሉ ምሳሌያዊ ንግግሮችን አስፍረዋል።
መላኩ ይርዳው የተባሉ ጸሐፊ ‘ደቦ ቅጽ-፩’ ከተሰኘው የ60 ደራሲያን ሥራዎችን ያካተተ መጽሐፍ ውስጥ ‘የሴትነት ጸጋ’ በሚል በጻፉት መጣጥፍ ሴትነትን ከፍቅር፣ ከጥበብ፣ ከብልሃትና ልዕልና ጋር አቆራኝተውታል።
 
“ሴት ልጅ ቅኔ ናት፤ ከተባለላት፣ ከተጻፈላት፣ ከተዜመላት በላይ የረቀቀች ረቂቅ ቅኔ ናት። እስከዛሬ ከያኒያን ስለሴት ከተራቀቁት፣ ከተጠበቡት ሁሉ እኔ ለማውቃት ሴት ሁሉ የሚመጥኑ ሆነው አልታዩኝም። የሴትነት ጸጋው ብዙ ነውና የሴትን ትክክለኛ ማንነት መርምረን አጥንተን የደረስንበት ውስጠ-ስሪቷን አጥንተን የተረዳነው አይመስለኝም።… ከታላቅነቷ፣ ከብልሃቷ፣ ከረቂቅነቷ፣ ከመግዛት አቅሟ፣ ከርህራሄዋ፣ ከሰላማዊነቷ ከሌሎችም አያሌ በረከቶች አንጻር ለሴት ልጅ የተደረገላት፣ የተነገረላትና የሆነላት ሁሉ ያንስብኛል”
 
ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ስለሴት ልጅ ጭቆና የታገለ እና ስለክብሯ የዘመረ ምሁር ነው። ስለሴት ልጅ ስቃይና ሰቆቃ አትቷል። ‘በናቴኮ ሴት ነኝ’ በሚለው መጽሐፉ ስንኞች እንምዘዝ!
…. ግማሽ አካሏ ወንድ በትምክህት ቢከዳት
ጧ! ብላ አለቀሰች አዛኝ ቢደርስላት፣

ብሶት ተጫጭኗት ምንም ሰው አልሆነች
በቀቢጸ ተስፋ ሕላዌንም ጠላች
ያገሬ ጭቁን ሴት መድኅን መላ ያጣች….!
‘ሔዋንያት የትውልድ ፋብሪካዎች ናቸው፤ እነሱ ባይኖሩ ዓለም ባዶ ትሆን ነበር’ እንዲል ፈላስፋው ሶቅራጥስ። ስለሴት (ግማደ ሰቧ ፍጡር) ግፍና በደል ገሞራው እንዲህ ይላል።
“መራራ ጭቆና በሰፈነበት ምዝብር ሕብረተሰብ ውስጥ ታፍነው የሚኖሩ ሔዋንያት ብሶታቸው፣ ፍዳቸው፣ በደላቸው፣ ጭንቀታቸውና መከራቸው እንደ ሰማዕታት ገድል እጥፍ ድርብ ነው…. አጉል ልማድ፣ ኋላቀር ባሕልና አድሃሪ ሕገ-ማኅበረሰብ ከከንቱ አስተሳሰቦች ጋር ተዳምሮ በአንድነት በመመሳጠር ዘርዓ ሔዋንን ሲጫወቱባቸው ሲያሾፉባቸው ኑረዋል” (ገጽ-23)
በሥነ-ሕይወት ሳይንስና በትምህርተ-ጄነቲክስ (አካለ ሕላዌ) ሴቶችን ከወንዶች የሚያሳንስ ምንም አይነት አካላዊ ተሰጥኦ እንደሌለ ተረጋግጧል። ታሪክና ተረክ ግን ወገንተኛ መሆኑን ገሞራው ይናገራል። ተረክና ተረት አልባሌ ታሪክ የሚፈጥሯቸው አርበኞች ሁሉ በፆታቸው ተባዕት በመሆናቸው፤ በሴቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደሩ ሊኖራቸው የሚችለው ዕድገት ላይ ትልቅ ደንቃራ ሆኖ መቆየቱን ይገልጻል። “የታሪክን ሁኔታዎችን የመመንዘር ትርጓሜያዊ አንጻር የታሪክን ትዕይንቶች ብንመረምር አንደርድሮ የሚያደርሰን ሴቶች ከወንዶች የከፋ ባህሪያዊ ድክመት እንዳለባቸው ከሚያሳይ ሥዕል ላይ ነው።”
በሚት(ተለጣጭ ተረክ) ላይ የሚራቀቁት አቶ ቴዎድሮስ ገብሬ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፎክለር መምህር) ‘ተረኮች እማዊ ሳይሆን አባዊ ናቸው’ በማለት ይህን ጉዳይ ያጠናክሩታል። “በሚት ውስጥ ገነው ከሚታዩ አበይት ማኅበራዊና ባህላዊ እውነታዎች መሃል አንዱ ፆታዊ ወገንተኝነት ነው። የሰማናቸው፣ ያነበብናቸው ሚታዊ ተረኮች በእጅጉ አባዊ ለሆኑ ሥርዓቶች (ፓትሪያርካል ሲስተምስ) ያደሩ፣ በአብዛኛው በተባዕት ተጋዳሊያን የተሞሉ ናቸው” ይላል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዶክተር ይሁኔ (በገፅ-401) ስለሰው ማንነት ቀረጻ በተመለከተ ከጥንት እስከ ዛሬ አከራካሪ የሆኑ ፈላስፎችን ክርክር ያነሳሉ። ይኸውም የሰው ልጅ ‘ማን ቀረጸኝ? ተፈጥሮ ወይስ ተሞክሮ?’ የሚለውን መከራከሪያ ጽንሰ-ሃሳብ ይፈትሻሉ። በዚህም “ሰዎች ሲፈጠሩ የሰውየውን ችሎታ ይዘው ነው” እና “የሰዎች ማንነት የሚቀረጸው ከውልደት በኋላ በተሞክሮ ወይም ከአካባቢ ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር ነው” የሚሉትን ሃሳቦች ወስደው ከእናት ሚና ጋር ያዛምዱታል። እናም እናት ‘በየትኛውም መደብ ልጅን አሳምራ ትቀርጻለች’ የሚል ድምዳሜ ሰጥተዋል።
 
“በየትኛውም መንገድ በሰው ልጅ ላይ የእናት ቀራፂነት ስለሚኖር ከተጽዕኖዋ ማምለጥ የሚቻል አይመስለኝም።… አካባቢም ሰውን ይሰራዋል የሚሉትም ከውልደት በፊትም ሆነ በኋላ ከተፈጥሮ ጋር የሚደረገው ውስብስብ መስተጋብር ‘ሰው’ በመሆን ላይ ጉልህ ሚና ይጫወታል” ይላሉ። በዚህ እሳቤ ሰው የወላጆቹም፤ የአካባቢውም ውጤት መሆኑን በግልጽ እንረዳለን” ይላሉ።
 
ሴቶች ከጥንት እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ማኅበረ-ባህላዊ እንዲሁም ለሰላምና ዕርቅ እሴቶች ጉልህ ሚና አላቸው። ሴቶች ያልተሳተፉበት ዘርፍ የለም። ከመሪነት፣ ጥበበኝነት፣ ከአገር ድንበር ጠባቂነትና የዲፕሎማሲያዊ ሚና… መጥቀስ ይቻላል። ሴቶች በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ በሰላምና ግጭት አፈታት ግንባር ቀደም ተሰሚነት አላቸው። ለአብነትም ሀደ ሲንቄ፣ በሶማሌ-ሔር፣ በሲዳማ-ያካ፣ በራያ ማኅበረሰብ ዱበርቲዎች፣ በስልጤ-ሴረን ባህል መጥቀስ ይቻላል።
ከሰሞኑ ባከበርነው የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ሴቶች ውለታ በወፍ በረር ማውሳት ይቻላል። የኢትዮጵያ ሴቶች ከሌላው ዓለም ሴቶች በተለየ የራሳቸው ቀለም ያላቸው፣ የአመራር ልምድ ያዳበሩ፣ የመወዳደሪያ ስነ-ልቦና ያላቸው፣ ችለው አሸንፈው ያሳዩ ናቸው። ሴቶች ድሉን በማስመዝገብ የተጫወቱትን ሚና ያህል፣ ገድላቸው በታሪክ በሚገባ አልተወሳም። ዶክተር አልማው ክፍሌ የተባሉ የታሪክ ምሁር በአንድ ወቅት ሚዲያ ላይ ቀርበው “በአድዋ ጦርነት ዘማቾች 75 በመቶ ሴቶች ነበሩ” ሲሉ ሰምቻለሁ። በአድዋ ጦርነት ሴቶች በተለያዩ ሙያዎች ተመድበው ከካምፕ እስከ ጦር ሜዳ ከመመገብ እስከ ማጀገን፣ ከማከም እስከ መዋጋት ድንቅ ሚና ተወጥተዋል። ድርብ ድርብርብ ኃላፊነት ይዘው የዘመቱ፣ ለወንዶችም ልብ፣ ሞራልና ወኔ አቀባዮች ነበሩ።
እቴጌ ጣይቱን መሰል የአድዋ ሴት የጦር ፊታውራሪዎች በርካታ ናቸው። ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ ወልደአረጋይ ‘ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ’ በተሰኘው መጽሐፋቸው የሴቶችን ሚና በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፡-
“እንዲህም እየሆነ፣ አጤ ምኒልክ ባዳራሹ እቴጌ ጣይቱ በእልፍኝ ባለሟሎችዎን ወይዛዝርቱን ይዘው ግብሩ አንድ ቀን ሳይጎድል፣ ይዘምታሉ። ከዘመቻ ላይ ጠጁ ማሩ አለመጉደሉ፣ ስለምንድነው ያልህ እንደሆነ ይህን ታሪክ መመልከት ነው። በስድስት ድንኳን እንጀራው ሲጋገር ሲያድር፣ በአራት ድንኳን ወጡ ሲሠራ ሲያድር፣ ጠጁ በቀንድ በኮዳ ደግሞ ሦስት መቶ ስድስት መቶ የሚሆን ገንቦኛ ሲጓዝ ግብሩ ይጎድል ይመስልሀል” (ገጽ-241)
ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም ‘ከአሜን ባሻገር’ በተሰኘ መጽሐፉ ‘ሴቶች በዋሉበት’ በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ሴቶች ተጋድሎና ሚና “ከቁስ ባሻገር ከልብ ያቀርባሉ” ይላቸዋል።
“ሴቶች ባዋላጅነት ከነበራቸው የማይተናነስ ሚና በጦር ሜዳ ተጫውተዋል። እናቶቻችን በጦር ወቅት፣ መሳሪያ ያቀርቡ ነበር። ምግብ ያቀርቡ ነበር። ሃሳብ ያቀርቡ ነበር። ልብ ያቀርቡ ነበር። ደስታ ያቀርቡ ነበር። ኧረ ምኑ ቅጡ። ሴቶች ባንድ በሙቀጫ ዙሪያ፣ ማኅበረሰቡን ኬሚስት፣ ገጣሚና የፖለቲካ ተንታኝ ሆነው ማገልገላቸውን ልብ እንበል” ይላል። (ገጽ-138)
ዶክተር ይሁኔ (በገጽ-14) በበኩላቸው እናቶችን ሩህሩሆች፣ አጉራሽና አልባሽ፣ የችግር ቤዛዎች፣ ሕይወት ዑደት አስቀጣዮች፣ የሕይወት መድኅኖች፣ ባለብዙ ጸጋዎች፣ መልካም ባህሪ አውራሾች፣… በማለት ገልጸውታል። መላ ሴቶችንም በእናቶች አተያይ ማየት እንደሚገባም እንዲሁ።
 
“እናትነት መልካም ገጽታዎችን ደራርቦ የያዘ የሴት ልጅ ትልቅ መገለጫ ነው። እናትነት ከፍ ያለ ሥልጣን ነው። እናትነት ጥልቅና ሰናይ ባህሪያት የሚፈልቁበት ምንጭ ነው። እናትነት የደግነት፣ የጥራት፣ የልህቀትና ተፈላጊነት ማሳያ ተምሳሌት ነው። እናትነት ሞት የማያደበዝዘው ኃያል መንፈስ ነው። እናትነት ከባድ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ነው። … እናትነት የሰላም፣ የመልካም ግንኙነትና እንክብካቤ መፍለቂያ አድባር ናት። እናትነት ሰፊና ጥልቅ የሕይወት ትምህርት ቤት ነው። እናትነት ሌሎች ከስቃይ ነፃ እንዲሆኑ፣ ምቾት እንዲሰማቸው በሚደረግ ትግል ውስጥ ዋጋ እየከፈሉ መኖር ነው”
 
በመቀጠልም የኢትዮጵያ እናቶችን ‘ጠቃሚ ነገር ሰጪዎች’ ይላቸዋል።
 
“እናቶች ሰው የመሆኛ ቅመሞች የሚጨለፍባቸው ባህር ናቸው። … ሕይወታዊ ስሪታችን ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን የወሰደው ከእናት ነው። ከእናት የምናገኘው ‘ማይቶኮንድሪያ’ (ማይቶኮንድሪያ የኃይል ማመንጫ ክፍል ሲሆን የምንመገበው ምግብ እየተቃጠለና ወደ አስፈላጊው ኃይል እየተቀየረ ሕይወትን ያንቀሳቅሳል) የምግብ ማቃጠያ ምድጃ ወይም ኃይል ማመንጫ ቤት ሆኖ ያገለግላል። … ብዙ መልካም ስብዕና መገለጫዎች ምንጫቸው የእናት ፍቅር፣ የመልካም ስብዕና እና የርህራሄ ምንጭ ነው” (ገጽ- 61)
 
ኢያሱ በካፋ ‘የኢያሱ በካፋ ወጎች’ በተሰኘው መጽሐፉ እናትነትን ማህጸንን፣ ምግብን፣ ትንፋሽን፣ ደም፣ ሥጋን እና ነፍስን ሰጥተው በረቂቅ ተፈጥሮ ሰውን ከመውለድ ባለፈ ፍቅራቸውን ዘላለማዊ ገደብ አልባ እና ዕልቆ-ቢስ እንደሆነ እንዲህ ገልጾታል።
“እናትነት ነፍስን ማካፈል ነው፤ እናትነት የማይደበዝዝ ዘላለማዊ ፍቅር መስጠት ነው፤ እናትነት ከራስ ሕልውና ይበልጥ ለልጅ ማሰብ ነው፤ እናትነት ፍፁም ወረት አልባ መሆን ነው። እናት ለልጇ ያላት ፍቅር አይነጥፍም፤ አይለወጥም። ለእናት ልጇ ሁሌም ልጇ ነው” (ገጽ-4)
እናትነት በቃላት ለመግለጽ እንደሚከብድ፤ በውለታ ማካካስ ይከብዳል። የእናት ውለታዋን መክፈል የሚችል ልጅ የለም። የእናት ፍቅርን ለመግለጽም በርካቶች አንደበታቸው ይተሳሰራል፤ ቃላት ይነጥፍባቸዋል፤ ስሜታቸውን መግራት ይሳናቸዋል።
 
ድምፃዊ እሱባለው ይታየው(የሺ) ‘ይናገራል ፎቶ’ በሚል እናትና አባቱን በገለጸበት ሙዚቃ የመጨረሻው ማጠንጠኛው ‘እወድሻለሁ/እወድሃለሁ’ ያለው፤ እንዲሁም ድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ ‘እናት ውለታዋ’ በተሰኘ ዘፈኗ ውስጥ (ዜማና ግጥም ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ)፤ “ወላጅ እናት እኮ ፍፁም በመንፈሷ፣ ልጇን ትወዳለች አብልጣ ከራሷ” እያለች በሚስረቀረቅ ድምጿ የምታንጎራጉረው ለዚህ ይመስላል።
 
ዕውቁ የቋንቋ ሊቅ የሻው ተሰማ (የኮተቤው) ‘የጥቁር አፈር ትሩፋቶች’ በተሰኘው መጽሐፉ (ገጽ-79) ‘መቀነትሽን አጥብቂ’ በሚል ርዕስ ባሰፈረው ረዘም ያለ ግጥም ሁለት አንጓዎች ብቻ ስንመዝ የእናትነት ውለታን መመለስ እንደሚሳን፤ የእናትነት ግብሯ ‘እናት’ የሚለው ቃል በራሱ እንደሚያንስባት ያትታል።

“ለዚህ ወሮታሽ አጸፋ፤ እናት ይልሻል አገሩ፤
እኔም እናቴ ብልሽ መች ሊመጥንሽ ዳሩ።

እናትነት ምጡቅ ነው፤ እናት ከመባል ይልቃል፤
የግብርሽ ስንክሳር ዚቁ፤ በስያሜ መች ያልቃል”… በማለት ይገልጸዋል።
 
መውጫ
ዶክተር ይሁኔ የሴት እና እናትን የነገዋን መንገድ ከሳይንስ አተያይ አንጽረው፤ ከማኅበረ-ፖለቲካ፤ ከማኅበረ-ባህል ከፍታዋ አመሳክረው፤ እናትና ሀገርን መጋመድ አመስጥረው መልእክታቸውን እንደ መውጫ አስፍረዋል። ለስንበት አንድ አንቀጽ እንወርውር!!
“የእናት ሀገር ህልውና ከእናቶች ሕይወት ጋር በቀጥተኛ ተዛምዶ አለው። የሰመረ ትውልድ ሊቀጠል የሚችለው በጥሩ ሁኔታ በተገነባ የእናቶች አቅም ነው። የእናቶች አቅም ሲገነባ የራሳቸውን አቅም ያውቃሉ፤ ምርጫቸውን በራሳቸው ይወስናሉ፤ እንዲሁም ለሚመጣው ማኅበራዊ ለውጥ የራሳቸውን አሻራ ያሳርፋሉ። ስለሆነም የእናቶችን አቅም ማጎልበት ትውልድን ማጎልበት ነው። እናቶች ላይ መሥራት ትውልድ ላይ መሥራት ነው”
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም