ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በሎጂስቲክስ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ብቃት ያለው የሰው ኃይል በማፍራት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው-የማሪታይም ባለስልጣን

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 29/2015 የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ዘርፍ አቅም በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የእቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር በ4ኛ ዙር የአሰልጣኞች ሥልጠና የወሰዱ 28 ባለሙያዎችን አስመርቋል።

ሰልጣኞች የወሰዱት ስልጠና በቀጣይ ዓለም አቀፍ የእቃ አስተላላፊዎች ሥልጠና /ፊያታ ዲፕሎማ/ መስጠት የሚያስችላቸው መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር የኋላሸት ጀመረ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በሎጅስቲክ ዘርፍ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን የአገልግሎት ልህቀት አነስተኛው መስፈርት ነው።


 

የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ዘርፈ በርካታ ፈተናዎች እንዳሉበት ጠቅሰው፤ ብቁ የሰው ኃይል እጥረትና የአቅም ውስንነት መኖር ለዘርፉ ዝቅተኛ አፈጻጸም ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ይህንን ለመቅረፍ ከተቋማት አደረጃጀት ጀምሮ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ የመሳሰሉ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደመሆነም አመልክተው የሎጂስቲክ ዘርፍ አገልግሎት ስርዓትን በማሻሻል ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግና ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ሊያግዙ እንደሚገባ አመላክተዋል።


 

የኢትዮጵያ የእቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር የዘርፉን ዋነኛ ማነቆ የሆነውን የእውቀት ክፍተት ለመሙላት እያደረገ ላለው ጠረት አመስግነው የኢትዮጵያ ማሪ ታይም ባለስልጣን የሎጂስትክስ አገልግሎቶችን የተሳለጡና እውቀት መር የሚያደርግ ስትራቴጂ በመተግበር ላይ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ የእቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኤልሳቤጥ ጌታሁን በበኩላቸው የሎጅስቲክስ ዘርፉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋነኛ ሞተር ቢሆንም ፈተናዎች እንዳሉበት ጠቅሰዋል።

የሀገሪቱንና ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓቱን የወጪና ገቢ ንግድ በማሳለጥ ረገድ ትልቅ ሚና ያለውን የሎጂስቲክስ አገልግሎት ማዘመን ለነገ የማይባል ስራ ነው ያሉት ኃላፊዋ ማኅበሩ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

ማኅበሩ እስካሁን 200 ሰልጣኞች ዓለም አቀፍ የፊያታ ዲፕሎማ እንዲያገኙ ማድረጉንና 140 ባለሙያዎችን የአሰልጣኞች ስልጠና ተመራቂዎች በሎጂስቲክስ ዘርፍ የሚስተዋለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር እንደሚቀይሩም አረጋግጠዋል።

ዘርፉ የኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ እንደመሆኑ መጠን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም