የኢትዮጵያ የእቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር የአሰልጣኞች ሥልጠና የወሰዱ ባለሙያዎችን አስመረቀ

823

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 28/2015 የኢትዮጵያ የእቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር 4 ዙር የአሰልጣኞች ሥልጠና የወሰዱ 28 ባለሙያዎችን አስመረቀ።

የአሰልጠኞች ሥልጠና የወሰዱት ሰልጣኞች በቀጣይ ዓለም አቀፍ የእቃ አስተላላፊዎች ሥልጠና /ፊያታ ዲፕሎማ/ መስጠት የሚያስችላቸው መሆኑ ተመላክቷል።


 

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር የኋላሸት ጀመረ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በሎጅስቲክ ዘርፍ የአገልግሎት ልህቀት አነስተኛው መስፈርት ነው።

ከዘርፉ ፈተናዎችም ዋነኛው የአቅም ውስንነት መሆኑን ገልጸው የሚከሰቱት ዝቅተኛ አፈጻጸሞች ከዚሁ የመነጨ መሆኑን አንስተዋል።

ባለሥልጣኑ ይህንን ለመቅረፍ ከተቋማት አደረጃጀት ጀምሮ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግና የመሳሰሉ ሥራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።

በዛሬው እለት የተመረቁ ሠልጣኞች በዘርፉ ያለውን ማነቆ በመፍታት በኩል ቁልፍ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ሊያግዙ እንደሚገባ አመላክተዋል።


 

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ኤልሳቤት ጌታሁን በበኩላቸው በሎጅስቲክ ዘርፍ ያለው የአቅም ውስንነት ዘርፉ እንዳያድግ ማድረጉን ገልጸዋል።

በንግድ ሥርዓት ውስጥ ሎጂስቲክ ዋነኛው መሆኑን ገልጸው በዘርፉ ያለውን የአቅም ውስንነት መቅረፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።


 

የዘርፉን አቅም ለማሳደግ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየሰጠ መሆኑን በመጠቆም።

ማኅበሩ እስካሁን 200 ሰልጣኞች ዓለም አቀፍ የፊያታ ዲፕሎማ እንዲያገኙ ማድረጉንና 140 ባለሙያዎችን ደግሞ ለዓለም አቀፍ አሰልጣኝነት ማብቃቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም