የፓኪስታን ባለኃብቶች ጨርቃ ጨርቅን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አሳይተዋል--አምባሳደር ጀማል በከር - ኢዜአ አማርኛ
የፓኪስታን ባለኃብቶች ጨርቃ ጨርቅን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አሳይተዋል--አምባሳደር ጀማል በከር
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 28/2015 የፓኪስታን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት እና በተደረገላቸው ገለጻ ጨርቃ ጨርቅን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ገለጹ።
የፓኪስታን ንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመጎብኘት ከትላንት በስቲያ ገብቷል።
ልዑኩ ትላንት በነበረው መርሃ-ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በተገኙበት በኢትዮጵያ ያሉ ኢንቨስትመንት አመራጮች ላይ ገለጻ ተደርጎለታል።
በዛሬው ዕለትም የቦሌ ለሚና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የጎበኙ ሲሆን ጨርቃ ጨርቅና ለመድሃኒት ፋብሪካ ዝግጁ የተደረጉ ቦታዎችን ጎብኝቷል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፓሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰን ጨምሮ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አመራሮች በጉብኝቱ ላይ ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የግል ባለኃብቱን ለማበረታታትና በኢንቨስትመንት ላይ ለማሳተፍ እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ዙሪያ ለባለሀብቶቹ ሰፊ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
በፓርኮቹ ውስጥ የተዘረጉ መሰረተ ልማቶች፣ የአንድ መስኮትና ሌሎች አገልግሎቶች ላይም ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን የፓኪስታን ባለኃብቶችም በፓርኮቹ ውስጥ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር ተወያይተዋል።
ባለሀብቶቹ በኢንዱስትሪዎች ያደረጉት ጉብኝት በሰው ኃይል፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ከነሳሷቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ጨርቃ ጨርቅን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን ነው አምባሳደር ጀማል የገለጹት።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ዝግጁ ለሆኑት አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እየተረገ መሆኑም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው መንግሥት የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በአሰራርና ፖሊሲ የታገዘ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም አዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑም በአውሮፓና ኤዥያ አገራት ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ረገድ ያላትን እምቅ አቅም የማብራራትና ባለሀብቶችን የመሳብ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
ኮርፖሬሽኑ የለማ መሬትና መሥሪያ ሼዶች ዝግጁ ማድረጉን ጠቁመው ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ባለኃብቶችን በአጭር ጊዜ ለማስተናገድ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን አመልክተዋል።
የፓኪስታን ንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ ቡድን መሪ ኢብራሂም ካሊድ ታዋብ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ባየነው ነገር በጣም ተደስተናል፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያየነው የተሟላ መሰረተ ልማት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።