ቀጥታ፡

በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ የተሰማሩ ዜጎችን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል የአሥር ዓመት ፍኖተ-ካርታ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 28/2015 በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ የተሰማሩ ዜጎችን አቅም ማሳደግ የሚያስችል የአሥር ዓመት ፍኖተ-ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ገለጸ። 

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት እየተዘጋጀ ያለውን ፍኖተ-ካርታ አስመልክቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የመጨረሻውን ግብዓት የመሰብሰቢያ ውይይት አድርጓል። 

ተቋሙ ፍኖተ-ካርታውን ከጀርመኑ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) ጋር በመተባበር ላለፉት ሦስት ዓመታት በጋራ በመሆን እንዳዘጋጀው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ፤ ፍኖተ-ካርታው የዘርፉን ተከታታይነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ ያለመ ነው። 

በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በዘላቂነት በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚል እሳቤ መዘጋጀቱንም ጨምረው ገልጸዋል። 

የመሰረተ-ልማት አለመሟላት፣ የብድር አቅርቦት ችግርና ምቹ የገበያ ትስስርን የተመለከቱ ክፍተቶችን ለመሙላት ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጳውሎስ በርጋ በበኩላቸው፤ የፍኖተ-ካርታው ተግባራዊ መሆን አምራቾች የሚገጥማቸውን ችግሮች የሚቀርፍ ነው። 

ፍኖተ-ካርታው በቀጣይ ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ አደረጃጀት የማስተካከል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

በውይይቱ የተሳተፉ የኤቲ ደብሊው ኢንጂነሪንግ ሥራ አስኪያጅ አይሸሽም ጥላሁን እንደተናገሩት፤ ፍኖተ-ካርታው መዘጋጀቱ ዘርፉን በአግባቡ ለመምራትና የዘርፉን ችግሮች ለማቃለል ወሳኝ ነው።  


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም