የአርቲዩር ረምቦ የጥበብ ስራዎችን የሚያሳይ አውደ ርዕይ በሐረር ከተማ ተከፈተ

445

ሐረር (ኢዜአ) የካቲት 28/2015 የአርቲዩር ረምቦ የጥበብ ስራዎችን የሚሳይ አውደ ርዕይ በሐረር ከተማ ተከፍቷል።

አርቲዩር ረምቦ .. ኦክቶበር 20/1855 በፈረንሳይ አገር አርዴን በሚባል ግዛት ውስጥ በምትገኘው ሻርልቪል ከተማ ውስጥ የተወለደ ሲሆን 1880 ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈበት እስከ 1891 ድረስ በኤደን (የመን) ሐረር (ኢትዮጵያ) ካይሮ (ግብፅ) እና በቀይ ባህር ወደቦች ዜይላ፣ አቦክ እና ታጁራ ውስጥ አሳልፏል።

በፈረንሳይ በስነ ግጥም ታላላቅ ከሚባሉት የብርሃን ፈርጦች መካከል አርቲዩር ረምቦ አንዱ ባለቅኔ መሆኑ ይጠቀሳል


 

የፈረንሳዩ ባለቅኔ አርቲዩር ረምቦ የጥበብ ስራዎቹን የሚያሳይ አውደ ርዕይ በሻርልቪል ሐረር አሶሲየሽን አማካይነት በከተማው በሚገኘው የፈረንሳዩ ባለቅኔ አርቲዩር ረምቦ የባህል ማዕከል ዛሬ ተከፍቷል።

በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የአሶሲየሽኑ ፕሬዝዳንት ሚስተር ዣን ፔር ሚኔ እንደተናገሩት፤ ባለቅኔው አርቲዩር ረምቦ የትውልድ ከተማ የሆነችው ሻርልቪል እና ሐረር ከተማ እህትማማች ናቸው።

ይህንንም ተከትሎ የአርቲዩር ረምቦን ስራዎች ለትውልድ ለማስተላለፍና ለመጠበቅ .. 2010 የሻርልቪል ሐረር አሶሴሽን ተመስርቶ የተለያዩ የእንክብካቤ፣ የድጋፍና የአቅም ግንባታ ስራዎች በጋራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።


 

አውደ ርዕዩም ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩ ባለፈ በአሶሲየሽኑና በክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ የአርቲዩር ረምቦን የጥበብ ስራዎችን ለትውልድ ለማስተላለፍና ለመጠበቅ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለዋል።

የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ አውደ ርዕዩ በክልሉ በሚገኙ መስህቦች ላይ እሴት ከመጨመሩ ባለፈ ለጎብኚዎች ምቹና ሳቢ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብለዋል።


 

በተጨማሪም በከተማው በሚገኘውን የፈረንሳዩ ባለቅኔ አርቲዩር ረምቦ የባህል ማዕከል የሚገኙ የጥበብ ስራዎቹን ለመንከባከብና ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚከናወነውን የጋራ ስራ ያጎለብታል ሲሉ ተናግረዋል።

በፈረንሳዩ ባለቅኔ አርቲዩር ረምቦ የባህል ማዕከል በተከፈተው አውደ ርዕይ በፈረንሳዩ ባለቅኔ የተጻፉ ስነ ግጥሞችና የራሱን ህይወት የገለጸባቸው ጽሁፎች፣ ስዕሎችና ሌሎች የጥበብ ስራዎች ለእይታ ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም