የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ከፍታ ለማስቀጠል ለአትሌቲክስ ስልጠና ማዕከላት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ከፍታ ለማስቀጠል ለአትሌቲክስ ስልጠና ማዕከላት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 28/2015 የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ከፍታ ለማስቀጠል በታዳጊ ስፖርተኞች ላይ ለሚሰሩ የስልጠና ማዕከላት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ከአትሌት አበበ ቢቂላ የጀመረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ድል በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬም በድንቅ አትሌቶቿ አሸናፊነት ታሪክ እየተመዘገበ እንደቀጠለ ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ከፍታ ለማስቀጠል በተለይም በታዳጊ ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ለዚህም በታዳጊዎች ስልጠና ላይ እየሰሩ የሚገኙ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላትን እየደገፈና እያበረታታ እንደሚገኝ ይገልጻል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን።
የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ዮሐንስ እንግዳ፤ የአትሌቶችን ድል በማስጠበቅ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማስቀጠል በታዳጊና ተተኪ ስፖርተኞች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የስልጠና ማዕከላት ሲከፈቱ እስከ 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑ የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ፣ አቋም የሚፈትሹበት ውድድር ማዘጋጀት፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠትና የቴክኒክ ድጋፎችንም በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ነው ተወካዩ የተናገሩት።
ለማሰልጠኛ ማዕከላቱ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጠቆም።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፋሲሊቲ እና አትሌቶች አገልግሎት የሰራ ሂደት መሪ አቶ አሰፋ በቀለ በበበኩላቸው ከሚገኙ ሰባት የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት መካከል በተያዘው ዓመት ለአምስቱ ሙሉ የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የበቆጂ፣ ጂንካ፣ ሀገረሰላም፣ የተንታና ደብረብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ድጋፍ የተደረገላቸው ማሰልጠኛዎች ናቸው።
የማይጨው አትሌቲክስ ማዕከልም ቀደም ሲል በነበረው ጦርነት ምክንያት አገልግሎቱ መቋረጡን ገልጸው፤ ወደ ስራ ሲመለስ የተለያዩ ድጋፎች ይደረግለታል ነው ያሉት አቶ አሰፋ።