ኢትዮጵያ እና ኩዌት በፖሊስ ተቋማት ያላቸውን ትብብርና ግንኙነት ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ኩዌት በፖሊስ ተቋማት ያላቸውን ትብብርና ግንኙነት ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ የካቲት 28/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ኩዌት በፖሊስ ተቋማትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ናይፍ ሃብስ አል ኡተይቢን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የሁለቱን ወዳጅ ሀገራት ፖሊሳዊ ግንኙነት አጠናክረው በማስቀጠል አብሮ ለመስራትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለብዙ ዘመናት የቆየ ከመሆኑ አንጻር ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት በትብብር መስራት ይገባቸዋል።
አምባሳደር ባየር አል ኦታይቢ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የድንበር ቁጥጥር አደረጃጀትን በሎጂስቲክስና በአቅም ግንባታ ለመደገፍ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ላይ ከተቋሙ ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግና ለማገዝ ቁርጠኝነታቸውን ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም በሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት የተጀመረውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረሙ በውይይቱ ወቅት መገለጹን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።