ቀጥታ፡

የፓኪስታን ባለሃብቶች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየጎበኙ ነው 

 

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 28/2015 የፓኪስታን ባለሃብቶች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየጎበኙ ነው። 

የፓኪስታን ንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመጎብኘት  ከትላንት በስቲያ ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል።
 
ልዑኩ ትላንት በነበረው መርሃ-ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በተገኙበት በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ገለጻ ተደርጎላቸዋል። 

በዛሬው ዕለትም ባለሃብቶቹ የቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመጎብኘት ላይ ናቸው።



 
በጉብኝቱ ላይ በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጀማል በከር፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፓሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰን ጨምሮ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አመራሮች ተገኝተዋል።
 
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ የኢትዮጵያ መንግሥት የግል  ባለሃብቱን በኢንቨስትመንት ላይ ለማሳተፍ  የሚያስችሉ  ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው።
 
በአሁኑ ወቅት 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ይሄው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።   

የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብተው ወደ ስራ ከገቡ ፓርኮች መካከል አንዱ ሲሆን ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ገብተው  ወደ አሜሪካና አውሮፓ ምርት እየላኩ መሆኑን  አብራርተዋል።  

ፓርኩ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆኑ የለማ መሬት እና ሼዶች እንዳሉትም ምክትል ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም