በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ መድን የዛሬ ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ መድን የዛሬ ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 28/2015 በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ መድን ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰአት በድሬዳዋ ስታዲየም ይከናወናል።
በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመራው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን በ32 ነጥብ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ይገኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ እስካሁን ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ዘጠኝ ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አምስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በ15 ጨዋታዎች 32 ግቦችን ሲያስቆጥር ዘጠኝ ግቦችን አስተናግዷል።
ፈረሰኞቹ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፉ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥተዋል።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ መድን በ30 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ኢትዮጵያ መድን እስከ አሁን ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ዘጠኙን ሲያሸንፍ፤ ሶስት ጊዜ ተሸንፎ፤ ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በ15 ጨዋታዎች 27 ግቦችን ሲያስቆጥር 21 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው የሁለቱን ክለቦች ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌላኛው የ16ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 10 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሲዳማ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ19 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በ18 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በተያያዘ ዜና ትናንት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሐዋሳ ከተማ ለገጣፎ ለገዳዲን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ዲቻ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።