ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በኢኮኖሚ መስኮችም ለማጠናከር ትሰራለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ የካቲት 27/2015 ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በኢኮኖሚ መስኮች ይበልጥ ለማጎልበት እንደምትሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በመጠቀም መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የፓኪስታን ባለሃብቶች የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የሁለቱ አገራት አምባሳደሮች፣የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ፣የፓኪስታን የኢንቨስትመንት እና ንግድ ልዑካን ቡድን አባላት እንዲሁም የኢትዮጵያ  የንግድ ዘርፍ ማህበራት አባላት ተሳትፈዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የልዑካን ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

መንግስት ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ አሰራሮችን በመተግበር ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በተለይም በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ እንዲጠቀሙ  ጥሪ ያቀረቡት አቶ ደመቀ በሁለቱ አገራት ያለውን ግንኙነት ዘርፈ ብዙ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በየኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ወደ ፓኪስታን የሚጀምረው በረራ የሁለቱን አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የልዑካን ቡድኑ የመጣበት ዓላማ እንዲሳካ መንግስት ክትትልና ደጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት፡፡


 

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሾዛብ አባስ በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነትን ይበልጥ በኢኮኖሚ መስክ ለማስተሳሰር እንደሚሰራና የልዑካን ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የዚሁ ስራ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

አገራቱ በግብርና ኃይል ልማት፣በማዕድን እና ሌሎች ዘርፎች ላይ በተለይም በግብርናው መስክ ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው በጋራ መስራት የሚችሉባቸው ሁኔታዎች አሉ ብለዋል። 

በተለይ ኢትዮጵያ ለመስኖ መልማት የሚችል ሰፊ ሃብት እንዳላት አመልክተዋል። 

የፓኪስታን ባለሀብቶች ልዑካ ቡድን አባል የሆኑት ኢብራሂም ፋይዝ፤ ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በአገሪቷ ያለውን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመመልከት መሆኑን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ ግዙፍ የሆነውን የአፍሪካ ገበያ እድል ለመጠቀም ዋና መግቢያ ናት" ብለዋል።


 

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በበኩላቸው ሁለቱ አገራት መልካም የሆነ  የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የልዑክ ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ደግሞ ግንኙነቱን በኢኮኖሚ መስክ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን ጨምሮ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ በርካታ ሁኔታዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም