በአርብቶ አደር አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም በቅድመ መከላከል ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአርብቶ አደር አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም በቅድመ መከላከል ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ የካቲት 27/2015 በአርብቶ አደር አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የቅድመ መከላከል ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ተመራማሪዎች ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ አገራት የሚገኙ አርብቶ አደሮችን በተመለከተ ሲያካሒዱት የቆዩትን ጥናት ይፋ አድርገዋል፡፡
ጥናቱ የተካሔደው "ፓስትረስ" በተባለ ፕሮጀክት አማካኝነት ሲሆን፤ የኢትየጵያ፣ ኬኒያ፣ ቱኒዚያ፣ ጣሊያን ቻይና እና ህንድ ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
ከተመራማሪዎች መካከል የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮችን በሚመለከት ጥናት ያደረጉት አቶ ማስረሻ ታየ፤ ለበርካታ ዓመታት ለአርብቶ አደሮች ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሰራቱ ምክንያት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች በተደጋጋሚ እንዲጋለጡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ለአርብቶ አደሩ የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ የንብረት ኢንሹራንስ እንዲያገኝ ማድረግ ፣ ድርቅን የሚቋቋሙ የእንስሳት ዝርያዎችን እና የሜትሮሎጂ አገልግሎቶችን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ በጥናቱ መመላከቱንም ተናግረዋል፡፡
የእንስሳት ሃብት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ድርሻው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ ተመራማሪ ጣሒራ መሐመድ ናቸው፡፡
በተለይ በምስራቅ አፍሪካ በድርቅ ምክንያት በርካታ እንስሳት እየሞቱ መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪዋ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ አርብቶ አደሩን ያማከለ አሰራር መከተል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ በመስጠት ረገድ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በድርቁ ምክንያት የሰው ህይወት አለመጥፋቱን ነው የተናገሩት፡፡
በተለይ በቦረና ዞን በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ በዘላቂነት በመቋቋም ረገድ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመሆን የውሃ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡።
በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ለማድረግ ከዓለም ባንክ ጋር የትብብር ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል።
የውሃ አቅርቦትን ማሻሻልን ጨምሮ የቅድመ መከላከል ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በአርብቶ አደር አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል፡፡