በሶማሌ ክልል ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ማሽኖች ግዢ የሚውል ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ቀርቧል- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ማሽኖች ግዢ የሚውል ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ቀርቧል- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ
ጅግጅጋ(ኢዜአ) የካቲት 27/2015 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሶማሌ ክልል ለሚገኙ 53 ኢንተርፕራይዞች ማሽኖች ግዢ የሚውል ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማቅረቡን አስታወቀ።
በባንኩ የጅግጅጋ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ወንዶሰን ተመስገን እንደገለጹት፤ የፋይናንስ ተቋሙ በሶማሌ ክልል ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የሊዝ ፋይናንስ ብድር ማቅረብ ከጀመረ ሶስት ዓመት ሆኖታል።
በነዚህ ሶስት ዓመታት ውስጥ ቅድመ ሁኔታውን ላሟሉ 53 ኢንተርፕራይዞች ለማሽኖች ግዢ የሚያስፈልጋቸውን 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብድር መቅረቡን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በቀረበው ብድር አማካኝነት እስካሁን ለ42 ኢንተርፕራይዞች ማሽኖች ገብተው በመተከል ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ለቀሪ 11 ኢንተርፕራይዞች የተገዙት ማሽኖች ጅቡቲ ወደብ ላይ መድረሳቸውን አመልክተዋል።
የሶማሌ ክልል የኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብራሂም አህመድ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአዳዲስ አምራች ኢንተርፕራይዞች በሊዝ ፋይናንስ ብድር በማቅረብ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
ኢንተርፕራይዞቹ በብድር የቀረበላቸው የማሽኖች ተከላ ስራ ሲያጠናቅቁ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ምርት ለማቅረብ እና ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው የተናገሩት አቶ ኢብራሂም ባንኩ በቀጣይ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ብድር በማመቻቸት የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
በተመቻቸላቸው ብድር ተጠቃሚ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ማከናወን እንደሚጠበቅባቸውም ነው አቶ ኢብራሂም ያሳሰቡት።