ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የጀመርነውን ድጋፍ እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የጀመርነውን ድጋፍ እናጠናክራለን
ደሴ (ኢዜአ) የካቲት 27/2015 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለግድቡ የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል እና ቅርስ አድን በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር በኮምቦልቻ ከተማ ለሕዳሴው ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አካሂደዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ አቶ ሁሴን ይመር ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን የአንድነት አርማ ከመሆኑ በላይ ሀገራዊ ልማት የሚያፋጥን ነው።
ከግድቡ ግንባታ ሥራ መጀመር አንስቶ ሁሉም በአቅሙ የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፣ በቀጣይ ግንባታው ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመሩትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ድረስ ከ7ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ሁሴን፣ በቀጣይም በቦንድ ግዥና በመለገስ ከእዚህ በላይ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ሌላዋ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዘውዲቱ አሊ በበኩላቸው "መንግስት የሕዳሴው ግድብ ከነበረበት ችግር አላቆ በተሻለ የግንባታ ሂደት ላይ በማድረሱ አስደስቶናል፤ በምንችለው ሁሉ ድጋፋችንን በማጠናከር እንጨርሰዋለን" ብለዋል።
ለግድቡ የውሃ ሙሊት ሥራ ከማከናወን ጎን ለጎን ኃይል እንዲያመነጭ መደረጉ የበለጠ ብርታትና ወኔ እንደሆናቸው የገለጹት ወይዘሮ ዘውዲቱ፣ "ግድቡን በጋራ እንደጀመርነው ሁሉ እንጨርሰዋለን" ብለዋል።
ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ እስካሁን ድረስ ከ3ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ በቀጣይም ቤተሰቦቻቸውን በማስተባበር ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወንድወሰን ልሳነወርቅ በበኩላቸው፣ የከተማውን ህዝብና የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ለሕዳሴ ግድቡ ግንባታ እስካሁን ድረስ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
"በቀጣይም የህዝቡን አንድነትና ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ ለግድቡ ግንባታ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ የድርሻውን ይወጣል" ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ እንቻለው ታደሰ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ሲያደርገው የነበረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
"ግድቡ በራሳችን አቅም የሚሰራ የጋራ ማንነታችንና ኩራታችን ነው" ያሉት አቶ እንቻለው፤ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያው ፋይዳው የላቅ በመሆኑ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁሉም መረባረብ እንዳለበት ገልጸዋል።
"ሕዳሴ ጉዞ ሁለት" በሚል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማነቃቃት፣ ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ ለህዝብ ለማሳወቅና ለማመስገን እንዲሁም ግንባታውን ለማፋጠን በተለያዩ ከተሞች የጉዞ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።
ከየካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለ45 ቀናት በሚካሄደው ጉዞ በ200 ከተሞች ላይ ንቅናቄ ለመፍጠር ታቅዶ ወደተግባር መገባቱንም አቶ እንቻለው ገልጸዋል።
በእዚህም ከቦንድ ግዥ በተጨማሪ በ"8100 A" አማካኝነት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን አስረድተዋል።
"ጀግኖች አባቶች በአንድነት ቆመው የመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነውን የአድዋ ድል እንዳስመዘገቡ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም የሕዳሴውን ግድብ በማጠናቀቅ የራሱን አዲስ ታሪክ መስራት አለበት" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል እና ቅርስ አድን በጎ አድራጎት ድርጅት የጉዞ ሁለት አስተባባሪ ኢንጂነር ነጮ ወርቁ ናቸው።
እስካሁን በተዘዋወሩባቸው ከተሞች ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎና ወኔ እንዳለ ማየታቸውን ገልጸው፣ በጉዞው ከዕቅድ በላይ ገቢ ለመሰብስብ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ የከተማው ነዋሪዎችና አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።