ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 22 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 27/ 2015 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከጀርመን ልማት ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ 22 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ድጋፍ አደረገ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ባንኩ ድጋፉን ያደረገው ከጀርመን ልማት ባንክ ባገኘው የ15 ሚሊዮን ዮሮ  የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘው ድጋፍም 79 ትራክተሮች ተገዝተው ለአርሶ አደሮች እንደሚያከፋፈሉ ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ ዛሬ 22 ትራክተሮችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ትራክተሮቹ በባንኩ "20 በ 80" የቁጠባ ዘዴ ለቆጠቡ አርሶ አደሮች መሰጠታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የድጋፉ አካል የሆኑ 9 ትራክተሮች ተገዝተው ለአርሶ አደሮች መከፋፈላቸውንም አስታውሰው፤ የቀሪ 48 ትራክተሮች ግዥ በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ትራክተሮቹ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ እንዲስፋፋ በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ በዘርፉ የተያዘውን የልማት ጉዞ ለማፋጠን እንደሚያግዙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የግብርና ዘርፉን በማገዝ ረገድ ከዚህ በፊት 300 ትራክተሮችና 100 ኮንባይነሮች ግዥ በመፈጸም ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረጉን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም